በቄለም ወለጋ የሁለት ግለሰቦችን ግጭት ወደ ብሄር ለመለወጥ የተደረገው ሙከራ ተገቶ ችግሩ በሰላም ተፈቷል

54
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 በቄለም ወለጋ ዞን የሁለት ግለሰቦች ግጭቱ ወደ ብሔር መልክ በመለወጥ ብጥብጥ ለመፍጠር የተሞከረው ድርጊት በአካባቢው ሽማግሌዎችና ወጣቶች በሰላም መፈታቱ ተገለፀ። ባለፈው ሐሙስ በኦሮሚያ ክልል ቄላም ወለጋ ዞን በሀዊ ገላን ወረዳ ልዩ ስሙ 'መቻራ' በተባለ ቀበሌ "ማሳዬ ውስጥ ገብተህ ጫቴን ወስደህብኛል" በሚል በሁለት ግለሰቦች መካከል የተነሳው ግጭት ለአንድ ሰው ሕይወትና ለሶስት ሰዎች አካል ጉዳት ዳርጓል። ይህን የግለሰቦች ግጭት ወድ ብሔር በመለወጥ የባሰ ብጥብጥ ለመፍጠር ተሞክሮ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸው፤ ይሁንና ድርጊቱ በአገር ሽማግሌዎችና በወጣቶች ጥረት የባሰ ችግር ሳያስከትል መፈታቱን አረጋግጠዋል። በ1977 ዓ.ም ጀምሮ በስፍራው መኖር የጀመሩት የአማራ ተወላጅ አቶ ኑሩ አሊ ለኢዜአ በስልክ በሰጡን መረጃ፤ በግጭት በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ስምንት ቤቶች ተቃጥለዋል። ነገር ግን በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎች አለመኖራቸውን ገልጸው፤ ችግሩ እንዳይባባስ የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ወጣቶች ርብርብ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። "ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በጋብቻና በደም ተሳስረን ለዓመታት በፍቅርና በወንድማማችነት አብረን ኖረናል" ያሉት አቶ ኑሩ፤ በግለሰቦች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለማባባስ የሞከሩ ሰዎች እንደነበሩ ግን አልሸሸጉም። የቀበሌው ሊቀ መንበር አቶ ግርማ ሙልዬ በበኩላቸው፤ በግለሰቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት በአካባቢው ህብረተሰብ፣ በአገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች እንዲሁም ወጣቶች ጥረት መፈታቱን አረጋግጠዋል። ህብረተሰቡ ባለፈው ቅዳሜ በነበረው ገበያ በሰላም ሲገበያይ ውሎ በሰላም ወደየቤቱ መመለሱን ለአብነት ያነሱት አቶ ግርማ፤ ወጣቶችም የብሔር ግጭት እንዳይቀሰቀስና ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ሚና እንደነበራቸውም ገልጸዋል። የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ምትኩ ለሜሳ በበኩላቸው የግለሰቦችን ግጭት ለዘመናት አብሮ በኖረው ሕዝብ መካከል ለመለኮስ ሲጥሩ የነበሩ ግለሰቦችን ወደ ሕግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። እስካሁንም ግጭቱን ለማባበስ የሞከሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አንስተዋል። ችግሩን ለመፍታት ዛሬ የወረዳው አስተዳዳሪ በተገኙበት ውይይት መካሄዱንና የእርቅ ስነ ስርዓት እንደሚኖር ተናግረዋል። በሀዊ ገላን ወረዳ ስር በሚገኙ አራት ቀበሌዎች በርካታ የአማራ ብሔር ተወላጆች ሀብትና ንብረት አፍርተው እንደሚኖሩ በሰላም እየኖሩ መሆኑን አቶ ምትኩ ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም