ወጣቱ የአድዋን አኩሪ ድል በመዘከር የሀገሪቱን አንድነት እንዲያስጠብቅ ተጠቆመ

380

ባሀር ዳር ጥር 15 ቀን 2012 ወጣቱ ትውልድ ጥንት አባቶች በአድዋ ያስመዘገቡትን አኩሪ ድል በመዘከር የሀገሪቱን አንድነትና ሰላም ማስጠበቅ እንዳለበት ተጠቆመ።
የዓደዋ የድል  በዓል ለማክበር መነሻቸውን ከአዲስ አበባ በማድረግ የተንቀሳቀሱ ሰባተኛው የአደዋ የሰላም ተጓዥ ወጣቶች ቡድን  ደብረብርሃን ከተማ ማምሻውን ገብተዋል።

በዚህ ወቅት የቡድኑ አስተባባሪ ወጣት በኃይሉ አድማሱ ለኢዜአ እንዳለው አድዋ ኢትዮጵያዊያን በመተባበር የኢጣሊያን ፋሽስት ጦርን የደመሰሱበት ታላቅ የድል በዓል ነው።

ጥንት አባቶች  ችግርን ተቋቁመው ወራሪውን ኃይል በተጋድሎ ድል በመንሳት በትውልድ ቅብብሎሽ የሀገሪቱን አንድነት ጠብቀው ማቆየታቸውን አውስቷል።

በዚህም ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን ተጋድሎ በመዘከርና ፈለጋቸውን በመከተል የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አንድነት በማስጠበቅ  የተጣለበትን አደራ መወጣት እንዳለበት ጠቁሟል።

የአደዋ የሰላም ተጓዥ ቡድን  ዓላማም በሚልፍበት ሁሉ ፍቅርን፣ ሰላምንና አንድነትን ለወጣቶች ማስተማር እንደሆነ አስተባባሪው ገልጿል።

የቡድኑ አባል ወጣት ቢኒያም ወንድወሰን በበኩሉ “ይህ ጉዞ የሀገርን ክብር ያስጠበቁ አባት አርበኞችን ለመዘከር እና ገድላቸውን ለማስታወስ ነው” ብሏል።

በጉዟቸው የሚያገኟቸውን ታሪካዊ ቦታዎችን በመጎብኘት ለሌላው ህብረተሰብ ለማስተዋወቅ  ጭምር እንደሆነም አመልክቷል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ  አቶ መርከብ ለማ  እንደገለጹት ወጣቶቹ የአባቶቻችን ታሪክ ለመዘከከር በእግር የሚያደርጉት ጉዞ በራሱ ታሪካዊ ነው።

በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ባለሃብቱን በማስተባባር ለተጓዥ ቡድኑ አባላት በቆይታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የአደዋ የሰላም የተጓዥ  ቡድኑ ከሐረር፣ አርባ ምንጭና አዳማ በመነሳት አዲስ አበባ የተሰባሰቡ  56 አባላት እንዳሉት  ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል።