ፕሮግራሙ 120 ሺህ አርሶ አደሮች በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ እያደረግኩ ነው አለ

64
ባሀር ዳር ጥር 15 ቀን 2012 በኢትዮጵያ 120 ሺህ አርሶ አደሮች በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የቤነፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም አስታወቁ። ፕሮግራሙ በባህርዳርና በወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ክላስተር ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ያከናወናቸወን ተግባራት በባህር ዳር ገምግሟል። በኢትዮጵያ የፕሮግራሙ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ቴዎድሮስ ተፈራ በመድረኩ እንዳስታወቁት ፕሮግራሙ የምግብ ዋስትና ክፍተት ያለባቸውን አርሶ አደሮች ከተረጂነት ለማውጣት እየሰራ ነው። ፕሮግራሙ 200 ሚሊዮን ብር በጀት እየተተገበረ ያለውም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው የተመረጡ 60 ወረዳዎች መሆኑንም አመልከተዋል። በፕሮግራሙ በሰብልና በእንስሳት ዘርፎች በሚከናወኑ ተግባራት ከ70 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረጉን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። አርሶ አደሮቹ በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ፣ ሥርዓተ ምግባቸው እንዲያሻሽሉና የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሳድጉ ተደርጓል ብለዋል። በተለይ ከምርምር ማዕከላት የሚለቀቁ የሰብልና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ከግብርና ሚኒስቴርና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ የማላመድና የቅድመ ማስፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የፕሮግራሙ አስተባባሪ ዶክተር አልማዝ ጊዜው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በሦስት ዞኖች የተሻሻሉ የሰብል ምርጥ ዝርያዎችን እንዲጠቀሙ፣ ለአቅም ግንባታና ቴክኖሎጂን በአገር በቀል ዕውቀት ለመተግበር ያደርጋል ብለዋል። በዚህም 32 የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች ከስድስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች መሰጠታቸውን አስረድተዋል። የክልሉ ግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን አቢታ እንደተናገሩት የባህርዳርና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ለ20 ወረዳዎች እገዛ በማድረግ ላይ ናቸው። ቢሮው ሥራውን ወደሌሎች ወረዳዎች ለማስፋት ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል። ፕሮግራሙ ከኔዘርላንድስ መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚተገበር ተመልክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም