ሁለተኛው የሳይንስ ሙዚዬም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተከፈተ

643

መቀሌ ጥር 15 / 2012  በኢትዮጵያ ሁለተኛው የሳይንስ ሙዚዬም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተከፈተ ::

ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሳይንስ  ዐውደ ጥናትም  ዛሬ ጀምሯል።

ሙዚዬሙ ማርክ ባልፍንድ የተባለ የአሜሪካ በጎ አድራጊ ድርጅት 305 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የውስጥ ቁሳቁስ  እንዳሟላለት  ተገልጿል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ የተከፈተ ሙዚዬምም ሆኗል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲው በሳይንስ መስክ ያሰናዳው ዓለም አቀፍ ዐውደ ጥናትም ተከፍቷል።

በዐውደ ጥናቱ ከአሜሪካ፣ አውሮፓ ፣እስያና አፍሪካ የሚገኙ የሳይንስ ማዕከላትና   የሳይንስ ሙዚዬም ዳይሬክተሮች ተሳትፈዋል።ጥናታዊ ጽሁፎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መላኩ አዳል እንዳሉት ሥራ ፈጣሪ ዜጎች ለማውጣት  የሳይንስ ፣የቴክኖሎጂ ፣የኢንጂነርንግና ሂሳብ ማእከላት ሚናቸው ጉልህ ነው ብለዋል።

አገሪቱ ሥራ ፈጣሪ ዜጎች ማውጣት አለባት ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በየዓመቱ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች በሳይንስ የዳበረ ዕውቀት እንዲኖራቸው የማዕከላቱ ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል።

የእሥራኤሉ ወይዚማኒ ሳይንስ ተቋም ዳይሬክተር ሮነን ሚር በበኩላቸው ዐውደ ጥናቱ ማዕከላቱ የልምድና የሃሳብ  ልውውጥ የሚያደርጉበት ከመሆኑም በላይ፤ የኢትዮጵያና የእሥራኤልን ግንኙነት ያሳድገዋል ብለዋል።

የአንድን አገር እድገት ቀጣይ ለማድረግ ሴቶችን በሳይንስ ያላቸውን ተሳትፎ  ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርሰውም ተናግረዋል።

የሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንጂነሪንግ ሂሳብ መንደር ኢኒሼቲቭ መስራች ዶክተር ዓለማየሁ ገብረ እግዚአብሄር እንዳሉት ዐውደ ጥናቱ የተዘጋጀው በሳይንስ የላቁ መምህራንና ተማሪዎች ለማሰልጠንና ትስስር ለመፍጠር ያመቻል ብለዋል።

ዐውደ ጥናቱ በአገሪቱ የሳይንስ ማዕከላትን ለማስፋፋት፣ጥራት ለመጠበቅና የሙያ ድጋፍ እንዲያደርጉ ያግዛል ያሉት ደግሞ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረ ሕይወት ናቸው።