ለውጡን የሚያስቀጥል አመራር ለማብቃት እየሰራሁ ነው--- የብልጽግና ፓርቲ

132
አዳማ አዜአ/ ጥር 15/2012 ለውጡን ማስቀጠልና ማሻገር የሚችል አመራር ለማብቃት እየሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ። በየደረጃው የሚገኙ በቁጥር 2ሺህ የሚጠጉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የሚሳተፉበት ስልጠና ነገ በአዳማ ከተማ  ይጀመራል። በፓርቲው የዴሞክራሲ ማዕከል ግንባታ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አወሉ አብዲ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሀገራዊ ሪፎርሙን ከዳር ለማድረስ እየተሰራ ነው። የስልጠናው ዓላማ ሀገሪቱ ያለችበትን ምዕራፍ በትክክል በመገንዘብ ለውጡን ማስቀጠልና ማሻገር የሚችል አመራር ለማብቃት ማመቻቸት መሆኑን ተናግረዋል። ስልጠናው በይዘቱ የተለየ ከመሆኑም ባለፈ ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የጋራ አቅጣጫና የማስፈጸሚያ ስልት የሚቀመጥበት እንደሆነ አስታውቀዋል። አቶ አወሉ እንዳሉት በሀገሪቱ የሚስተዋሉ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ፣የፓርቲው መሠረታዊ መርሆች፣ዓላማና ፕሮግራሞች በስልጠናው ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። "አመራሩ ይህን ተገንዝቦ በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን፣የህዝብ ደህንነትና ልማት ማስቀጠል ብሎም ለውጡን ለማሻገር ትጥቅና ስንቅ የሚሆንለትን ግብዓት የሚያገኝበት ነው" ብለዋል። ራሱን ባከሰመው የኢህአዴግ የነበሩ ችግሮችን ከመሰረቱ ለማስወገድና አዲስ በተፈጠረው ውህድ ፓርቲ አቅጣጫዎች ላይ አመራሩ ግልጽ ግንዛቤ ይዞ ከብልጽግና መሠረታዊ መርሆች ጋር ራሱን መቃኘት እንዲችል ለማዘጋጀት እንደሆነም ገልጸዋል። በተለይ የመደመር እሳቤና ይዘቱ፣ሀገሪቱ የጀመረችው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞች ለማሳካት የሚችል ጠንካራ አመራር ለመፍጠር በክህሎት፣አመለካከትና እውቀት ለማሰናዳትም እንዲሁ። በአዳማ ከተማ ነገ የሚጀመረው ስልጠና ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ መሆኑን  አቶ አወሉ አብዲ አመልክተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም