በነባር የስኳር ፋብሪካዎች እየተከናወኑ ባሉ የለውጥ ስራዎች በወጪ ቅነሳና ምርታማነት ማሳደግ ውጤት እየታየ ነው ተባለ

125

አዲስ አበባ ጥር 15/2012 (ኢዜአ) ”ባለፈው አንድ ዓመት በነባር የስኳር ፋብሪካዎች እየተከናወኑ ባሉ የለውጥ ስራዎች በወጪ ቅነሳና ምርታማነት ማሳደግ ውጤት እየመጣ ነው” ሲል የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ለማሽን ጥገና ሊወጣ የነበረ 150 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉ ተጠቁሟል።

የመገናኛ ብዙሃንና የመንግስት አካላት የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክትን በመጎብኘት ላይ ናቸው።

ኢዜአ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባን በነባር ስኳር ፋብሪካዎች ላይ እየተካሄዱ ስላሉ የለውጥ ስራዎች ዙሪያ አነጋግሯል።

አቶ ወዮ ባለፈው አንድ ዓመት ኮርፖሬሽኑ ነባር የስኳር ፋብሪካዎች ላይ ሲከናወኑ የነበሩ የለውጥ ስራዎች በሶስት ጉዳዮች ላይ ማተኮራቸውን ይገልጻሉ።

የክረምት የፋብሪካ ማሽነሪዎች ጥገና ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ የማድረግ፣ ፋብሪካዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ወደ ስራ እንዲገቡና በቂ የሰው ሃይል እንዲመደብላቸው ማድረግ እንዲሁም በአገር ውስጥ ባለሙያዎች የማሽነሪዎች ጥገና ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የማፍያ ጋን (ቦይለር) ላይ ጥገና ለማካሄድ በግልጽ ጨረታ 150 ሚሊዮን ብር ተጠይቆ እንደነበር አውስተዋል።

ጥገናውን ግን በአገር ውስጥ ባለሙያዎች በመጠገን ሊወጣ የነበረውን ወጪ ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ከዚህ በፊት በቀን ያመርት የነበረው አምስት ሺህ ኩንታል ገደማ የስኳር ምርት አሁን ከዘጠኝ እስከ አስር ሺህ ኩንታል መድረሱን አመልክተዋል።

ከፊንጫ ውጪ ወንጂ ሸዋና መተሐራ የስኳር ፋብሪካዎችም ለውጥ እያሳዩ ከሚገኙ ፋብሪካዎች መካከል እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም ችግር የነበረውን የስኳር ዘርፍ ባለሙያዎች እጥረት ለመፍታት በዘርፉ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ስልጠና መጀመሩ ትልቅ እመርታ መሆኑንም ጠቁመዋል።