የተፈጠሮ ሃብት ልማት ስራ ምርታማናት እንዲያድግ እያገዘ ነው….አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

566

ደሴ ጥር 15/ 2012 (ኢዜአ)  በኢትዮጰያ እየተከናወነ ያለው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ስራ ለሰብል ምርታማነትና ለደን ሽፋን ማደግ አጋዥ እየሆነ መምጣቱን እንደተመለከቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።
የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዙሪያ ከደቡብ ወሎ ዞን አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በደሴ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ከኢኮኖሚያዊ ድህነት ለመውጣተት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዉ ትርጉም ያለው ለውጥ በሚያመጣ አግባብ መከናወን ይኖርበታል።

በአያያዝና በአጠቃቀም ጉድለት ለበረሃማነት የተጋለጡ አካባቢዎችን በአፈርና ዉሃ ጥበቃ ሥራ መልሶ ማልማት የህልውና አጀንዳ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባም ገልፀዋል።

በሃገሪቱ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ደን በአጠቃቀም መዛባት ለከፋ ጉዳት ተጋልጧል ያሉት አቶ ገዱ በዚህም በረሃማነት እየተስፋፋ በምርታማነት ላይ ተጽኖ ሲያሳድር መቆየቱን አመልክተዋል።

የችግሩን አሳሳቢነት መንግስት በመረዳቱ ባለፉት ዓመታት የህዝቡን ጉልበት በመጠቀም አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ የደን ሃብቱ መልሶ ማገገም እንደጀመረ ማስተዋላቸውን ጠቅሰዋል።

የተሰሩ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎችም የሰብል ምርታማነት እንዲጨምር እገዛ ማድረጋቸውን፤ደርቀው የነበሩ የውሃ አካላት መልሰው መማንጨት መጀመራቸውንም አብራርተዋል።

“በተለይ ወሎ የመልክዓምድሩ አቀማመጡ አስቸጋሪ በመሆኑ በተፈጥሮ ሀብት ስራ በተደረገዉ ጥረት ተጨባጭ ለዉጥ መምጣቱን ጠቁመዉ፤ ተሞክሮዉን በተለያዩ አካባቢዎች ማስፋት ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያለ ጥቅም ስራ የፈቱ መሬቶችን እንደየ ባህሪያቸዉ ማልማት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በዘንድሮዉ የተፈጥሮ ሀብት ስራም በተለዩ ተፋሰሶች ኮረብታማ፣ ገደላማ፣ ቦረቦርና የተራቆቱ መሬቶች በማልማት፣ ሳርና ችግኝ በመትከል ወደ አረንጓዴ በመቀየር የደን ሽፋኑን ለማሳደግ ሁሉም የየድርሻዉን እዲወጣ አሳስበዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ በበኩላቸዉ እንደተናገሩት በዘንድሮዉ የተፈጥሮ ሀብት ልማት 600 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የተጎዱ መሬቶች ላይ የአፍርና ዉሃ ጥበቃ ስራ ይከናወናል፡፡

ከአንድ ሺህ በላይ በሚሆኑ ተፋሰሶች 630 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ተለይቶ ቅድም ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከዚህ በፊት በተሰሩ ልማቶች ጠቀሜታዉን በተጨባጭ በማየቱም የተጎዱ መሬቶችን በመንከባከብ ምርታማነቱን እያሳደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

“የተሻለ ዉጤት ያስመዘገቡ ወረዳዎችን ተሞክሮ በማስፋት ክትልና ድጋፍ ይደረጋል” ብለዋል፡፡

የመቅደላ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ልዑል ሰገድ አድማሱ በበኩላቸዉ በ70 ተፋሰሶች 42 ሺህ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 65 ሺህ ሄክታር ለማልማት ቅደመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

“ህብረተሰቡም ጠቀሜታዉን ተረድቶ በራሱ ተነሳሽነት የአፍርና ዉሃ ጥበቃ ስራ እያከናወነ ነዉ”ብለዋል፡፡

በዉይይቱ የ24ቱም ወረዳ አመራሮች፤ የግብርና ባለሙያዎች፤ ከክልልና ከፌዴራል የተዉጣጡ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።