የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ለአምስት የማዕድን ምርመራ ኩባንያዎች ፍቃድ ሰጠ

240
አዲስ አበባ ጥር 15/2012 (ኢዜአ) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማዕድናት ፍለጋና ምርመራ ለማካሄድ የፈቃድ መውሰጃ መስፈርቶችን አሟልተው ከቀረቡ አምስት የማዕድን ኩባንያዎች ጋር የፍቃድ ውል በመስጠት ስምምነት ተፈራረመ። በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶን ጨምሮ የሚኒስቴሩ፣ የደቡብና የአማራ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲዎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል። ኩባንያዎቹ ፍቃድ ያገኙት በወርቅ፣ በብረትና ብረት-ነክ ማዕድናት እና “በራዮላይት ዳይሜንሽን ስቶን” የማዕድናት አይነቶች ላይ ምርመራ ለማድረግ ነው። ከእነዚህም አለታ ላንድ ኮፊ በብረት ምርመራና በማርብል፣ ሮዝ ኢትዮጵያ በወርቅ፣ አጎዳዮ ሜታልስ በብረት  እና ኤዋን ማርብል ኤንድ ግራናይት በማርብል ማዕድናት ፈቃድ ወስደዋል። የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ  በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ፈቃድ አሰጣጡ በማዕድን ዘርፉ የአሰራር ስርዓት መሠረት የተከናወነ ነው። በምርመራ ወቅትም ቅድሚያ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጤና፣ ለአካባቢ ደህንነት፣ በዘርፉ ዕውቀት ላላቸው  ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል ቅድሚያ መስጠት የሚሉ መስፈርቶችም በስምምነቱ ላይ መካተታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ፈቃድ ወስደው በጸጥታ ችግር የተነሳ ስራ ለማቆም የተገደዱ አካባቢዎችን ወደስራ ለማስገባት  ከክልሎች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ዘርፉ የሚያጋጥሙት ችግሮችን ለመፍታትና ውጤታማ ለመሆኑን ሚኒስቴሩ የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ ስለመሆኑ  ነው የተናገሩት ዶክተር ሳሙኤል፤ የፈቃድ አሰጣጥ ስምምነት ሲፈጸም ክልሎችን የማሳተፍ ተግባር መጀመሩን ተናግረዋል። ዶክተር ሳሙኤል አክለውም፤ የክልሎችም ፍላጎትና ጥያቄም የአካባቢውን ማህበረሰብ ተሳታፊ እንዲያደርግና አካባቢያቸውን እንዳይጎዳ እንጂ ሌላ ያለመሆኑን አብራርተዋል። የፈቃድ ውሉ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ስራቸውን ሲያቋርጡም ሰዎችን ጨምሮ በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ማናቸውንም ቅሬታዎች እንዲወገዱ የሚያስገድድ መሆኑ ተገልጿል። ኩባንያዎቹ ለኢንቨስትመንት ወጪ የሚሆን 44 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የመደቡ ሲሆን በቆይታቸውም በስራ  ዕድል ፈጠራው 30 ጊዜያዊና 27 ቋሚ በጠቅላላው ለ57 ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድሎችን እንደሚያመቻቹ ተጠቅሷል። ሁሉም ፈቃድ የወሰዱት ኩባንያዎች በዘርፉ ልምድ ያላቸው የግል ኩባንያዎች መሆናቸውም ተጠቁሟል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም