የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሁለት ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ

248

አዲስ አበባ ጥር 15/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲና የስፖርት ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 7ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በአግባቡ እንዲመራ ለማድረግ በኤጀንሲ ደረጃ እንዲቋቋም የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ ተቀብሎ አጽድቆታል።

አዋጁ በከተማዋ የሚገኙ ሕጻናትና ወጣት ተማሪዎች በምግብና በትምህርት ግብዓት አቅርቦት ችግር ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማና ብቁ ዜጋ ሆነው አገራቸውን እንዲረከቡ ለሚደረገው የሰው ሃብት ልማት ፕሮግራም መሳካት አስተዳደሩና ሕብረተሰቡ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት አሰራር ለመዘርጋትም እንዲሁ።

የተጀመረውን የምገባና የትምህርት ግብዓት አቅርቦት አሰራር ተቋማዊና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል ኤጀንሲው በአዋጅ እንዲቋቋም መደረጉ ተጠቅሷል።

ይህም የምገባና የግብዓት አቅርቦት አሰራሩ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ይረዳል ነው የተባለው።

ምክር ቤቱ ሌላው በዛሬ ውሎው የተወያየው የከተማዋን የስፖርት ኮሚሽን ተጠሪነት ለማሻሻል በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው።

እስካሁን የከተማ አስተዳደሩ የስፖርት ኮሚሽን በሚል ስያሜ የሚጠራው ተቋም ተጠሪነቱ ለወጣቶች በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ እንዲሆን መደረጉ ተልዕኮውን በሚገባ እንዳይወጣ አድርጎታል ነው የተባለው።

ኮሚሽኑ በየደረጃው ባለው መዋቅር ከፍተኛ አመራር ለሆነው የከተማዋ ካቢኔ ጉዳዮችን እያስወሰነ መስራት ባለመቻሉ ችግሮች ሲፈጠሩበት መቆየቱ ተነስቷል።

እያደገ የመጣውን የዓለምና የአገር አቀፍ እንዲሁም የመዲናዋን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የስፖርት መዝናኛ እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ ስፖርት ለልማት፣ ለሠላምና አንድነት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ታሳቢ ያደረገ አደረጃጀት መፍጠር ማስፈለጉም ተነግሯል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ በቀረበለት የስፖርት ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል።

ምክር ቤቱ ነገም በሚቀጥለው ስብሰባው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንና የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ መስሪያ ቤቶችን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም እንደሚያደምጥ ይጠበቃል።

የከተማ አስተዳደሩ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅና የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብ ላይም ይወያያል ተብሏል።