ህንድ ለኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ድጋፍ እያደረገች ነው

5250

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2012  ህንድ በኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚንቀሰቃሱ ተቋማትን አቅም ለማጎልበት እየሰራች መሆኗን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር አኑራ ስሪቫስታቫ ገለጹ።

ህንድ ሕገ-መንግሥት ያረቀቀችበትንና ሙሉ ለሙሉ ሕዝባዊ መንግሥት የመሰረተችበትን ቀን በኢትዮጵያ የህንድ ኤምባሲ እየተከበረ ነው።

ጎን ለጎንም ኤምባሲው ኢትዮጵያና ህንድ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩበትን 70ኛ ዓመት ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ አምባሳደሮች ጋር ዛሬ አክብሯል።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኑራ ስሪቫስታቫ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የረጅም ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያና ህንድ በትምህርትና በጤና ዘርፍ የጎላ ትብብር አላቸው።

”በትምህርት ዘርፍ ያለውን ትብብር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይገነዘበዋል” ያሉት አምባሳደሩ፤ በጤና ዘርፍ ህንድ ለኢትዮጵያዊያን የጤና ፍላጎት በዋጋና በጥራት ተመራጭ መዳረሻ መሆኗ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የሁለቱ አገሮች አጋርነት በሌሎችም የትብብር መስኮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይበልጥ እየተስፋፋና እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።

ለአብነትም ከወራት በፊት የተቋቋመውን የህንድና የኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ትብብር መርኃ ግብርን ጠቅሰው ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

የትብብር ማዕቀፉን ተከትሎ 26 የህንድ የዘርፉ ተቋማት ከኢትዮጵያ ሁለት አቻ ተቋማት የአቅም ማጎልበቻ ትብብር ማድረግ መቻላቸውን ገልጸዋል።

በመጪዎቹ ስድስት ወራት ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው የዘርፉ ተቋማት በኢትዮጵያ ይፈጠራሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው አምባሳደሩ ገልጸቀዋል።

በተጨማሪም ኤምባሲው በቅርቡ ባቋቋመው የጤና ማዕከል 500 የከንፈር መሰንጠቅ ችግር ያጋጠማቸው ኢትዮጵያዊ በነጻ ህክምና ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

በቅርቡም ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የመድሃኒት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ዓመቱ የተሳካ የሁለትዮሽ ግንኙነት የተደረገበት እንደነበር አምባሳደሩ አንስተዋል።