የደቡብ ክልል የአስተዳደራዊ አደረጃጃት ኮሚቴ አባላት ከወገንተኝነት የጸዳ መፍትሄ ይዞ የመምጣት ዝግጁነት እንዳላቸው ገለጹ

92

አዲስ አበባ ጥር 15/2012 (ኢዜአ)  ''ከአካባቢያዊ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ለደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚበጅ የመፍትሄ ሃሳብ ይዘን ለመምጣት ዝግጁ ነን'' ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአስተዳደራዊ አደረጃጃት ኮሚቴ አባላት ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሁሉም ወረዳዎች ከተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር ትናንት መወያየታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ በክልሉ ነዋሪዎች ለተነሱ የአስተዳደራዊ አደረጃጃት ጥያቄዎች የመፍትሔ ሃሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ ማዋቀሩን ይፋ አድርገዋል።

የኮሚቴው አባላት ከሁሉም የክልሉ ብሔሮች የተወከሉ ግለሰቦች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ስራቸውን በገለልተኝነትና በኃላፊነት እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።

ኢዜአ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሳሰቢያ አስመልክቶ የኮሚቴውን አባላት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስና አቶ ደበበ ባሩድን አነጋግሯል።

አባላቱ  በዚህን ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸውን የአደረጃጃት ለውጥ ጥያቄ የክልሉን ተወላጆች ባሳተፈ መንገድ በሰላም ለመፍታት ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል።

ዶክተር አሸብር እንዳሉት፤ በክልሉ የሚኖሩ ዜጎች ዘመናትን በተሻገረው የአብሮነት ታሪካቸው በርካታ የጋራ እሴቶችን አጎልብተዋል።

''ነገር ግን አገልግሎትን በቅርበት ከማግኘትና በፍትሃዊነት ከመልማት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የአስተዳደራዊ አደረጃጃት ለውጥ ጥያቄዎች እየተነሱ መጥተዋል'' ብለዋል።

በመሆኑም ለጥያቄዎች መፍትሄ እንዲቀርብ የተዋቀረው ኮሚቴ 'ከራስ ችግር ባለፈ ለክልሉ ህዝቦች ምን ይበጃል' በሚል እሳቤ እንደሚሰራ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝብ ጥያቄዎቹን ለመመለስ ቁርጠኛ የሆነ መሪ አግኝቷል ያሉት ዶክተር አሸብር፤ ማህበረሰቡ  በሰከነ ውይይት ለችግሮቹ መፈታት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በተገለጸው አግባብ መንቀሳቀስ  ከተቻለ ለጥያቄዎቹ መፍትሔ ማበጀት ቀላል መሆኑን በመጠቆም።

''ኮሚቴው ከእኔነት ወጥቶ የክልሉ ህዝቦች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መፍትሄ ማምጣት ይጠበቅበታል'' ያሉት ደግሞ ሌላው የኮሚቴው አባል አቶ ደበበ ባሩድ ናቸው።

ኮሚቴው ይህን እውን ለማድረግ እስከታችኛው የክልሉ መዋቅር ወርዶ የህብረተሰቡን ሀሳብ ለማድመጥ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

ስለክልሉ ያገባኛል የሚሉ አካላት ያልተገቡ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ተቆጥበው አሉን የሚሏቸው ሃሳቦች ለኮሚቴው ማቅረብ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

የአስተዳደራዊ አደረጃጃት ጥያቄ በባህሪው ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ሁኔታዎችን በትዕግስት እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም