የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ግንባታው የተቋረጠውን የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ በሚመለከት ውሳኔ እየጠበቀ መሆኑን አስታወቀ

61
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ግንባታው የተቋረጠውን የያዩ ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ በሚመለከት የመንግስትን ውሳኔ እየጠበቀ መሆኑን አስታወቀ። ኮርፖሬሽኑ ባለፉት 11 ወራት ያከናወናቸው ተግባራትን  በሚመለከት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስገመገመበት ወቅት እንዳስታወቀው የያዩ ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በተያዘለት እቅድ መሰረት ሊጠናቀቅ አልቻለም። የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ደሜ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንደተናገሩት፤ የማዳበሪያ ፋብሪካውን ግንባታ በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እቅድ ቢያዝም እቅዱ ሳይሳካ ቀርቷል። ፕሮጀክቱን የያዘው የብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የግንባታው ሂደት በሚጠናቀቅበት በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱን 50 በመቶ እንኳ ማድረስ እንዳልቻለ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። 44 በመቶ ደረጃ ላይ ግንባታው የቆመው ፋብሪካው በወር እስከ 90 ሚሊዮን ብር ወለድ ወጭ እያስወጣ ከመሆኑም በላይ ከአርሶ አደሮች ካሳ ጋር በተያያዘ ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉበት ተገልጿል። የውጭ ምንዛሬ፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግሮች የፋብሪካውን ግንባታ እንዲጓተትና እንዲቆም ያደረጉ ምክንያቶች እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ በተጨማሪ ባቱ ኮስቲክ ሶዳ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ መግባቱና ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካም በሙሉ አቅሙ እየሰራ እንዳልሆነ ተገልጿል። የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባደረገው የመስክ ምልከታና በኮርፖሬሽኑ ሪፖርት መሰረት በቀጣይ መጎልበት ያለባቸውንና መታረም ያለባቸውን እንዲለዩ አድርጓል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረእግዚአብሔር አርአያ የካይዘን ትግበራንና ወጪ ቅነሳን በሚመለከት ኮርፖሬሽኑ ጥሩ ተሞክሮ እንደነበረው ጠቅሰዋል። ብድር በመመለስና በዕቅድ መሰረት ተግባራትን በመፈጸም ረገድ ከፍተኛ ችግር እንዳለበትም ተጠቅሷል። በኬሚካል ዘርፍ የተገኘውን ውጤት በሚመለከት የ11 ወራት የእቅድ ክንውኑ ከ9 ወራት ክንውን ያነሰ በመሆኑ ተዓማኒነት የለውም ብሏል ቋሚ ኮሚቴው። ሰልፈሪክ አሲድን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ቢያዝም አፈጻጸሙ 3 በመቶ ብቻ በመሆኑ ምርቱን ለአገር ውስጥ እንኳን ማቅረብ ባለመቻሉ በቀጣይ በጀት ዓመት እንዲስተካከል ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። ኮርፖሬሽኑ የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት በ2011 በጀት ዓመት ጠንክሮ እንዲሰራ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበዋል። ኮርፖሬሽኑ ያላከናወናቸውን ተግባራት በ2011 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ፈቃዱ ደሜ የቀጣዩን ዓመት እቅድ ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም