በአገራዊው የሕዝብና ቤት ቆጠራ አካል ጉዳተኞች በአግባቡ እንዲቆጠሩ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው

60
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2012 በቀጣዩ አገራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ አካል ጉዳተኞች በአግባቡ እንዲቆጠሩ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄዱት ልዩ የጋራ ስብሰባ አራተኛው ዙር የሕዝብና ቤት ቆጠራ በአንድ ዓመት እንዲራዘም መወሰኑ ይታወሳል። ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የሕዝብና ቤት ቆጠራዎች አካል ጉዳተኞች በትክክል እየተቆጠርን አይደለም፤ በዚህ ሳቢያም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ሌሎችም ተጠቃሚ እየሆንን አይደለም ሲሉ ቅሬታ ያነሳሉ። ለኢትዮጵያ ዘላቂ እድገት አካል ጉዳተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ የአሳታፊነት ስርዓት ሊኖር እንደሚገባ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች መከታተያ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ሲሳይ ጥላሁን ይገልጻሉ። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ በኢትዮጵያ 864 ሺህ 218 አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ቢገልጽም ቁጥሩ ከዚህ በላይ እንደሚልቅም ያነሳሉ። አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ አሃዛዊ መረጃዎች የተደራጁ አለመሆናቸውንና ያለውን እውነታ በተጨባጭ እንደማያሳዩ ጠቁመዋል። ባለፉት ሶስት የሕዝብና ቤት ቆጠራዎች አካል ጉዳተኞች በትክክል አልተቆጠርንም የሚሉ ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ሲያነሱ እንደነበርም አውስተዋል። ይሄን ችግር ለመፍታት ከሚያስችሉ መፍትሔዎች አንዱ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በመሆኑ በቀጣዩ ቆጠራ አካል ጉዳተኞች በአግባቡ እንዲቆጠሩ ማድረግ ነው ብለዋል። በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ ለአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ለክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል። የሚሰጡት ስልጠናዎች ባለድርሻ አካላቱ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ መረጃዎችን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እንዲሰበስቡ ግንዛቤ መፍጠር እንደሆነም ነው አቶ ሲሳይ ያስረዱት። ስልጠናው የአካል ጉዳተኞች የጉዳት አይነት፣ ጾታ፣ ቁጥር የመሳሰሉት ጉዳዮችን ያካተተ ነው ብለዋል። በተለያዩ የአካል ጉዳተኞች አይነት የተቋቋሙ ማህበራት በአገር አቀፍ ደረጃ በስራቸው የሚገኙ አባላትን በመቁጠር አሃዛዊ መረጃዎችን የመሰብሰብ ስራ እያከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ አካል ጉዳተኞችም በትክክል እንዲታወቁ ለየተቋማቱ ተወካዮች ስልጠና ለመስጠት መታቀዱንም እንዲሁ። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በየተቋማቸው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እንዲታወቅ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ እንዲሰሩ ሚኒስቴሩ ትብብሩን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል። የትምህርት ተቋማቱ ጥናትና ምርምር በማድረግ አካል ጉዳተኞቹ እንዳይቆጠሩ እንቅፋት የሆኑ ምክንያቶችንና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የማስቀመጥ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል። እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ ከወዲሁ የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር በትክክል ለማወቅ የሚሰሩ ስራዎች ካለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ እንዲቆጠሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ። ኢትዮጵያ በ2002 ዓ.ም ባጸደቀችው የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን አገራት አካል ጉዳተኞችን በትክክል በመቁጠር በየጊዜው መረጃዎችን ይፋ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ያም ቢሆን ኢትዮጵያ ስለ አካል ጉዳተኞች በቂ አሃዛዊ መረጃዎችን ከመሰብሰብ አንጻር የሚፈለገውን ያህል እንዳልሰራችና በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም