ለአካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ለሚሹ ተማሪዎች የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነው ተባለ

391
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2012 ለአካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ለሚሹ ተማሪዎች የአካቶ ትምህርት ስርዓት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ ተገለጸ። የልዩ ፍላጎት ትምህርት ማለት ከመደበኛ ትምህርት በተለየ ሁኔታ ልዩ ትምህርት ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች እንደ እውቀታቸው መጠንና አስፈላጊነት ተዘጋጅቶ የሚሰጥ የትምህርት አይነት ነው። የልዩ ፍላጎት ትምህርት ራሱን በቻለ ትምህርት ቤት ወይም በመደበኛ ትምህርት ቤት ውስጥ በሚገኙ የልዩ ፍላጎት ትምህርት መስጫ ክፍሎች ወይም በመደበኛ ትምህርት ቤት በመደበኛ ክፍሎች ውስጥ በልዩ ፍላጎት ትምህርት መምህር ይሰጣል። በኢትዮጵያ የልዩ ፍላጎት ትምህርት በ1917 ዓ.ም እንደተጀመረ መረጃዎች ያመላክታሉ። የአካል ጉዳተኞችን መብትና ክብር መጠበቅን ዓላማ ያደረገው የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነትን የመንግስታቱ ድርጅት እ.አ.አ በ2006 ባደረገው 61ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ማጽደቁ ይታወቃል። ኢትዮጵያም ስምምነቱን በ1999 ዓ.ም ፈርማ በ2002 ዓ.ም አዋጅ ቁጥር 672/2002 በሚል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጽድቃዋለች። ይህ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት 50 አንቀጾች አሉት። የስምምነቱ አንቀጽ 24 አገራት ለአካል ጉዳተኞች የመማር መብት እውቅና መስጠት እንዳለባቸውና ያለምንም አድልዎ የትምህርት አገልግሎት ተደራሽነትን ማግኘት እንዳለባቸው ያስቀምጣል። አገራት በስርዓተ ትምህርታቸው የአካቶ ትምህርት ስርዓትን ማካተት እንዳላባቸውም ይገልጻል። የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንትና የህግ ባለሙያ አቶ ወሰን አለሙ ኢትዮጵያ በስምምነቱ መሰረት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ እየከወነች ያለው ስራ አነስተኛ የሚባል ነው ይላሉ። ለዓይነ ስውራን መማሪያ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች አለመሟላት፣ የልዩ ፍላጎት መምህራን ቁጥር ማነስ፣ የመማሪያ ቦታዎች ለተማሪዎች ምቹ አለመሆንና የአመለካከት ችግሮችን ዘርዝረዋል። በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አገራት ለአካል ጉዳተኞች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማሟላት ቢኖርባቸውም ከዚህ አኳያ በመንግስት በኩል አስፈላጊው ግዢ እየተፈጸመ አይደለም ብለዋል። በየትምህርት ቤቶች ያሉ የልዩ ፍላጎት መምህራን ቁጥር አነስተኛ በመሆኑም አካል ጉዳተኞች በሚገባና በሚመጥናቸው መልኩ ትምህርት እያገኙ አይደለም ባይ ናቸው። እንደ አቶ ወሰን ገለጻ አስገዳጅ ህግ ባለመኖሩ ትምህርት ቤቶች በተለይም የግል ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት የሚሹ ተማሪዎችን አንቀበልም ሲሉ የሚወሰድባቸው እርምጃም የለም። ይህ ጉዳይ በተለይ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኛ ህጻናት ተማሪዎች ላይ እንደሚብስ ጠቁመዋል። አካል ጉዳተኞችን ያላሳተፈ ስራ ቢሰራ ውጤት ማምጣት የማይቻል በመሆኑ ከዚህ አንጻር መንግስትና ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ትኩረት ለአካል ጉዳተኞች ሊሰጡ ይገባልም ብለዋል። የትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል ቡድን መሪ አቶ አለማየሁ ወልደቂርቆስ በቅድመ መደበኛ ትምህርት የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች 1 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ድርሻ እንደያዙ ይናገራሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት 11 በመቶ፣ በሁለተኛ ደረጃ 2 ነጥብ 8 በመቶ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የልዩ ትምህርት ፍላጎት እንደሚያገኙም ተናግረዋል። ያለው የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተደራሽነትም በጣም አነስተኛ እንደሆነ ነው የገለጹት። ተደራሽነቱን ዝቅ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት በጣም የተዛባና ጤናማ ባለመሆኑ አካል ጉዳተኞች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ማድረጉ ነው ብለዋል። አካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎችን የሚቀበሉ ትምህርት ቤቶች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑና ያሉትም በበቂ ሁኔታ አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ የአካል ጉዳተኞች የትምህርት መጠነ ማቋረጥ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ስምምነትን ትፈጽም እንጂ አስገዳጅ የሆነውን የስምምነቱን ማስፈጸሚያ ደንብ አልፈረመችም ብለዋል። የማስፈጸሚያ ደንቡ ባለመፈረሙ ምክንያት ትምህርትን ጨምሮ አካል ጉዳተኞች የሚገባቸውን አገልግሎቶች እያገኙ እንዳልሆነም ነው አቶ አለማየሁ ያስረዱት። በቂ በጀት አለመኖርም ሌላው ችግር እንደሆነ በመጠቆም። የስምምነቱን ማስፈጸሚያ ደንብ ለመፈረምና ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት 'የመንግስት አመራሮች ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት በጣም አስፈላጊ ነው' ብለዋል። በመንግስት በኩል የልዩ ትምህርት ፍላጎት ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ እንዳለና ይህን ማስፈጸም የሚያስችል ሰነድ በሚኒስቴሩ በኩል እየተዘጋጀ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የልዩ ትምህርት ፍላጎት ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱንና የሚመለከተው አካል ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። በትምህርት ሚኒስቴር ያለውን የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል ወደ ዳይሬክቶሬት የማሳደግ እቅድ ለሚኒስቴሩ ሃላፊዎች ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሆነም እንዲሁ። አካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ዜጎች በአካቶ ትምህርት ስርዓት የማስተማር ጉዳይም ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ እንደሆነም ተናግረዋል። ክልሎችም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ከመስራት አኳያ ያለባቸውን ክፍተት በመድፈን ለተደራሽነቱ በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው ብለዋል። ማህበረሰቡም ለአካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ክብር መስጠት እንደሚገባውና በሚገባቸው መልኩ ትምህርት እንዲሰጥ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም