የ”ዳራሮ” በዓል በማስመልከት የጽዳት ዘመቻና ሩጫ ተካሄደ

678

ዲላ ጥር 15/2012  (ኢዜአ)   የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ የ”ዳራሮ “ በዓልን ምክንያት በማድረግ የጽዳት ዘመቻ እና የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በዲላ ከተማ ተካሄደ።
በዚህም ወጣቶች ፣የፖሊስ አባላት፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ሌሎችም የህብረተብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

በጽዳት ዘመቻው ከተሳተፉት መካከል ወጣት ተመስገን ከበደ በሰጠው አስተያየት  በዓሉን በማስመልከት ለሁለት ሳምንታት ያህል ቆሻሻንና የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን በማጽዳት መሳተፉን ተናግሯል።

ጽዳቱ ለበዓሉ ብቻ ሳይሆን ለከተማው ውበት አስተዋጾኦ እንዳለው ገልጾ ወጣቶች በከተማቸው ልማት የነቃ ተሳትፏቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ጠቁሟል።

የዲላ ከተማ ፖሊስ አባል ሳጅን አሻግሬ ወልዴሚካኤ በበኩላቸው ከጸጥታ ስራቸው  በተጓዳኝ በከተማው የጽዳት ዘመቻ ተሳታፊ በመሆናቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢን ጽዳት ከተማውን ንጹህ በማድረግ የጤና ችግር እንዳይኖር አስተዋጾው እንዳለው ጠቅሰው በቀጣይም የዲላን ልማት ለማፋጠን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በዞን ደረጃ ጥር 16/2012ዓ.ም ለሚከበረው የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ትግሉ በቀለ ናቸው።

በተለይ በበዓሉ ለመታደም ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አመልክተው የጽዳት ዘመቻው የዝግጅቱ አካል መሆኑን አስረድተዋል።

ከተማውን ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረጉ ሥራ በበጋ ወራት በጎ ፍቃድኛ ወጣቶች በመደበኛነት እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የ”ዳራሮ “ በዓል ምክንያት በማድረግ የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በዲላ ከተማ ተኳሄዷል።

በሩጫው በአዋቂና ህጻናት በሁለቱም ጾታዎች ተሳትፈዋል።

በውድድሩ ላሸነፉ አትሌቶች ሽልማት የሰጡት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈው የጎዳና ላይ ሩጫው ለበዓሉ ድምቀት መስጠቱን ገልጸዋል።

የ”ዳራሮ” በዓል ማጠቃለያም ነገ በዲላ ስታዲየም እንደሚከበር ጠቁመዋል።

በዓሉም በድምቀት እንዲከበር የከተማው ነዋሪ እንግዶችን በመቀበል ከጸጥታው አካል ጋር በመተባበርና በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንዲወጡም አቶ ገዙ አቶ ገዙ ጥሪ አቅርበዋል።