በአርሲ ዞን የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ እየተካሄደ ነው

119
አዳማ ጥር 15/2012፡-(ኢዜአ )  በአርሲ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ገለጸ። ከጥር 13 ቀን 2012 ጀምሮ  እየተካሄደ ያለው ይሄው ስራ በዞኑ በተመረጡ አስር የገጠር ወረዳዎች ውስጥ ነው። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አባቡ ዋቆ እንዳሉት  ወረዳዎቹ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ሳቢያ ለችግር የተጋለጡ ናቸው። የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ መካሄዱ ድርቅን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን በአካባቢዎቹ ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል። ለአንድ ወር በሚቆየው በዚሁ ተግባር በ120 ተፋሰሶች የአፈርና ውሃ እቀባ ፣የአፈርና የድንጋይ እርከ ስራዎች እንዲሁም  የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች እንደሚዘጋጁ ይጠበቃል። የአርሲ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተካለ ቶሎሳ በበኩላቸው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ የሁሉንም አካላት ተሳትፎ ስለሚጠይቅ ህብረተሰቡን በተደራጀ አግባብ ለማንቀሳቀስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ ውጤት መገኘቱን የተናገሩት ደግሞ  የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው። ደርቀው የነበሩ ኩሬዎች ውሃ ማፍለቃቸውን፣ ተመናምነው የቆዩ እጸዋት መለምለማቸው ከተገኙት ውጤቶች መካከል ጠቅሰዋል። ተሰደው የነበሩ የተለያየ አእዋፍ ተመልሰው መምጣታቸውንና የደን ስፍራዎች አረንጓዴነት መላበሳቸውን ሌላው ውጤት እንደሆነ  አቶ እንዳልካቸው አውስተዋል። በዚህም የአርሶና አርብቶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አስተዋጽኦ አደርጓል። ይህንን ውጤት ዘንድሮም ለማስቀጠል በ6 ሺህ 400 ተፋሰሶችና ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለማካሄድ ታቅዶ ስራ ውስጥ መገባቱን አብራርተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም