በበጋ መስኖ የሚለማው መሬት መጠን ትክክለኛ ልኬት ተለየ

82
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2012 በበጋው የመስኖ ልማት የሚለማው መሬት መጠን ልኬት ትክክለኛው ቁጥር በዘመናዊ መሳሪያ ተለይቶ ወደ ስራ መገባቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። ከዚህ ቀደም በነበረው የመሬት መጠን ልኬት ችግር የተነሳ የሪፖርት ግሽበት በተደጋጋሚ ያጋጥም እንደነበር ተጠቁሟል። ባለፉት ዓመታት በበጋ መስኖ ልማት ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ ይነገር ነበር። በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ገርማሜ ጋሩማ  እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ በመስኖ የሚለማው መሬት መጠን ልኬት ትክክል አልነበረም። በበጋ መስኖ ሊለማ ይችላል ተብሎ ይገመት የነበረው የመሬት መጠን ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ሲሆን በዘመናዊ መሳሪያ ድጋፍ በተካሄደ ጥናት በበጋ መስኖ መልማት የሚችለው የመሬት መጠን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። አሁን በጂፒኤስ የታገዘ ጥናት በመደረጉ በበጋ የመስኖ ልማት በአገሪቱ የሚለማው መሬት በ800 ሺህ ሄክታር መሬት ዝቅ እንዲል አድርጎታል። ከዚህ ቀደም ከቀበሌዎችና ከወረዳዎች በተሰበሰበ መረጃ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረውን የመሬት ስፋት በመውስድ ለፖሊሲ አውጭዎችና ለተቋሙ የእቅድ መተግበሪያ እንዲሁም ለሌሎች ተግባራት ሲውል መቆየቱን ጠቁመዋል። ''በዘመናዊ  መሳሪያ ታግዞ የተሰራው የመሬት ልኬት የተስተካከለ ሪፖርት ለማቅረብና ለፖሊሲ ግብዓትነት  የሚውሉ አሳሳች ሪፖርቶችን ለመቀነስ ይረዳል'' ብለዋል። በተስተካከለው ልኬት በ2012 ዓ.ም የበጋ መስኖ ልማት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እየለማ ሲሆን ከ120 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ታቅዶ እየተሰራ ነው። እስካሁን 836 ሺህ ሔክታር በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 860 ሺህ ኩንታል ምርት ተገኝቶ ወደ ገበያ መቀረቡን አስታውቋል። ለዘንድሮ የመስኖ ልማት ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን የጣለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብም ለመስኖ ልማት ስራው ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል። ''በአገሪቱ የመስኖ ልማት እየተለመደ መምጣት ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ አገሪቱ በምግብ እህል ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት ያጠናክራል'' ብለዋል። በመላው አገሪቱ በመስኖ የሚለማ ከሶስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም