በቻይና የተከሰተው የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ቅድመ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2012 በቅርቡ በቻይና የተከሰተው ኖቭል ኮሮና 2019 የተባለ የመተንፈሻ አካልን የሚጎዳ ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ቅድመ ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የአለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮላ ቫይረስ በሽታ ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና ውሃን ክልል መከሰቱን አስታውቋል። ቫይረሱ ቀደም ብሎ የሚታወቅ በሽታ አምጪ ተህዋስ ቢሆንም በቻይና የተከሰተው ግን አዲስ የቫይረስ አይነት ነው ተብሏል። ቫይረሱ ከተከሰተበት ጀምሮ እስከ ዛሬ ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ 830 ታማሚዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 26 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል። የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ''የቫይረሱ ዝርያ ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ላይ ጉዳት የሚያስከትል ነው'' ብለዋል። ከዚህም ባለፈ ቫይረሱ በፍጥነት የመዛመት አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ የቻይና አጎራባች በሆኑ ጃፓን፣ ታይላንድ፣ ደቡብ ኮሪያ እንዲሁም ሲንጋፖር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል። በአሜሪካም አንድ ሰው ላይ በሽታው እንደተገኘ የአለም ጤና ድርጅት ማረጋገጡን የገለጹት ዶክተር ኤባ፤ ''ኢትዮጵያና ቻይና ካላቸው ጠንካራ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት አኳያ ቫይረሱ የሚገባባቸው ዕድሎች ሰፊ ናቸው'' ብለዋል። ለዚህም ከቻይና የሚመጡ ተሳፋሪዎች ላይ ምርመራ መደረግ መጀመሩን አመልክተዋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቮላን ጨምሮ ተመሳሳይ ቫይረሶች ላይ ቅድመ ምርመራ ለማድረግ የተዘጋጁ ቦታዎች ለዚሁ አገልግሎት እንደሚውሉ ዶክተር ኤባ ገልጸዋል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቢኖሩ እንኳን ለይቶ የማቆያ ስፍራ መዘጋጀቱንና የክትትልና ቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ጥቁር አንበሳና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች በጊዜያዊነት የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ዶክተር ኤባ ያብራሩት። በአሁን ጊዜ በሽታው በኢትዮጵያ ስጋት ባይሆንም በሽታ አምጪ ህዋሱ ጉንፋንና የመሳሰሉ በሽታ አምጪ ቫይረሶች የሚያሳዩት አይነት ከፍተኛ ትኩሳት የሚያሳይ በመሆኑ ተመሳሳይ ምልክቶች ያለባቸውና ከቻይና ጋር የቅርብ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ዜጎች በአፋጣኝ መመርመር እንዳለባቸው አሳስበዋል። ''ከቻይና ውጪ በሽታው የተገኘባቸው አገሮች 10 ቢሆኑም ባለው አለም ዓቀፍ አሰራር ከቻይና በሚመጡ መንገደኞች ብቻ ነው የቅድመ ምርመራ ስራው እየተደረገ ያለው'' ብለዋል ዶክተር ኤባ። በቻይና በመጀመሪያ የበሽታው ምልክት የታየው በውሃን ከተማ የባህል ምግቦች በሚያዘጋጁ ሰዎች ላይ ነው። በበሽታው የተያዙ ሰዎች  ትኩሳት ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ይታይባቸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም