የምርምር ማዕከሉ የደጋማ አካባቢ አትክልትና ፍራፍሬ ምርምር ውጤቶችን ለአርሶ አደሮች ለማድረስ እየሰራ ነው

99
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2012  የደብረ ብርሐን ግብርና ምርምር ማዕከል የደጋማ አካባቢ አትክልትና ፍራፍሬ ምርምር ውጤቶችን ለአርሶ አደሮች ለማድረስ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። የአትክልትና ፍራፍሬ ምርምር ክፍል ባልደረባ አቶ ፍስሃ ደሳለኝ ለኢዜአ እንዳሉት በማዕከሉ አምስት የምርምር ጣቢያዎች በአትክልት፣ ፍራፍሬና ስራስር ሰብሎች የዝርያ ማሻሻል ስራዎችን እየሰራ ነው። ከፍራፍሬ ምርምሮች መካከል በደጋማ አካባቢ የሚላመዱ ፍራፍሬዎችን ምርምር ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ  እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከእነዚህ መካከል 34 ዓይነት የአፕል፣ 10 አይነት የኮክ፣ 8 አይነት የፕለምና 9 አይነት የፒር ዝርያዎች ላይ ምርምር የማድረግ፣ የማላመድና የተላመዱትን የማባዛት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በቆላማ እንጂ በደጋማ አካባቢ የፍራፍሬ መስክ የተለመደ አለመሆኑን ገልጸዋል። ማዕከሉ ከቆላማ ፍራፍሬዎች ባሻገር በደጋማ አካባቢ የሚላመዱ ዝርያዎችን ከውጭ በማምጣት በማላመድና በማሻሻል አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ የፍራፍሬ መንደር ምስረታ መጀመሩንም ነው የገለጹት። የደጋማ አካባቢ ፍራፍሬዎች በአየር ጠባይና በበሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ክትትል እንደሚጠይቁ ተናግረዋል። የማዕከሉ የረጅም ጊዜ ዕቅድ አርሶ አደሮች በአትክልትና ፍራፍሬ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ማስቻል ነው ብለዋል። የምርምር ማዕከሉ የፋይናንስና የገንዘብ ውስንነት ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም ከሌሎች የምርምር ተቋማትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም