ቀለም፣ ዘመንና አገር

568

አየለ ያረጋል (ኢዜአ)

አገሬ ትለያለች-ለምሳሌ በ13 ወራት ጸጋዋ። ሁሉም አውራኅ፣ እያንዳንዱ ወራት በራሳቸው ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቀለማትን ይጎናጸፋሉ። የወራቱ ቅላሜና ሕብርነት ልዩ መልክዓ-ኢትዮጵያን ይፈጥራል። ከዘመን መባቻው መስከረም እስከ ማዕዶተ-ዘመኗ ጷጉሜን ወራቱ በሰማይና በምድሩ ተፈጥሯዊ፣ በባሕላዊና መንፈሳዊ ውቅራቸው ግላዊ ገጽታ ይነበብባቸዋል። የአገሬ ወራት ስያሜ ከመልክና ግብራቸው ይመነጫል። እናም አገር በወራት፣ ወራትም በቀለማት ይገለጻሉ።

አሁን አውራኁ ሐጋይ ነው። ሐጋይ ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25 ሦስት የበጋ ወራትን ይሸፍናል። ወሩም የሐጋይ አውራኅ መባቻው ወርኃ-ጥር ነው። ሊቃውንተ አበው የጥርን ስያሜ የትመጣነት ሲፈቱት ‘ጠረየ’ ከሚለው የግእዝ ግስ መምጣቱን፣ ትርጓሜውንም ‘መሰብሰብ፣ መመርመር፣ መፈለግ’ ይሉታል፤ የገበሬው የጥሪት መሰብሰቢያ ነውና። ዘመነ አስተርእዮ፤ ዘመነ ጥምቀት (ኤጲፋኒያ) ነውና ‘የመገለጥ፣ የመታየት ወር’ም ይሉታል። የሠርግ ወቅት ነውና ‘ዘመነ መርዓዊ ወይም ዘመነ ሙሽራ’ ሲሉም ያመሰጥሩታል።

ጥር የበጋ አውራኅ ቤተሰብ ነውና መዓልተ ሰማዩ የደመና ጋቢውን ይራቆታል። በሌሊት ከዋክብትና ጨረቃ በተራቆተው ሰማይ ላይ ይደምቃሉ። ትዕይንቱን ‘ወፍ የመሰለች ጨረቃ’ እንዲሉት። የኢትዮጵያ ምድርና ወንዞች ግርማቸውን ያጣሉ። አልፎ አልፎ ከሚታዩ የጥቢ አዝመራዎች በስተቀር ሐመልማላዊ ምድሩ ለዛውን ተቀምቶ ቅጠላ ቅጠሉ ይረግፋል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ጥር በኢትዮጵያዊ ለዛ፣ ጥበብና ቀለም የሚሞሸርበት ወር ነው። በተለይ መንፈሳዊና ባሕላዊ ገፅታው ጥርን ከኢትዮጵዊያን አልፎ ባዕዳንን ያስናፍቃል። ‘መልክዓ ጥር’ን በቀላሉ መግለጽ ቢከብድም በወፍ በረር መቃኘት ይቻላል።

የጥር ዐቢይ ኀይማኖታዊና ባህላዊ ድምቀቱ ‘ጥምቀት’ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምሮ የኢየሱስ ክርስቶስን ‘ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መውረድና በዕደ-ዮሐንስ መጠመቅን ትዕምርቱ ያደረገው ከከተራ እስከ ባሕረ ጥምቀት ያለው ስርዓትና ክዋኔ ልዩ ነው። በየትኛውም ዓለም የሚከወን የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ከሚፈፀመው ስርዓተ-ጥምቀት ጋር የሚነጻጸር፣ ማራኪና ትውፊት አዘል እንዳልሆነ በየአገሮቹ ተዘዋውረው የተመለከቱ እንግዶች የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። ጥምቀት ኢትዮጵያዊ ባህልን፣ መንፈሳዊነትን፣ ትውፊትን፣ ዕውቀትን፣ አገርኛ ጥበብ የሚጎላበት፣ አገር የውበት አክሊል የምትደፋበት ዕለት ነው።

ጥምቀት የዓለማችን የማይዳሰስ የኢትዮጵያ ወካይ ቅርስ መዝገብ ስር ሰፍሯል። ቅርሱ በተመዘገበ በሳምንታት ልዩነት የተከበረው የዘንድሮው በዓለ ጥምቀት በልዩ ድምቀት ‘መልክዓ ኢትዮጵያ’ን አጉልቶ አለፈ። በቀደምትነት ክርስትናን ከተቀበሉ አገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ጥምቀትን በ1530 ዓ.ም ገደማ በአጼ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግስት በአደባባይ፣ በሜዳና ወንዝ ዳር በአዋጅ መከበር ጀምሯል።

ጥር 10 ታቦታቱ ወደ ባሕረ ጥምቀት ወርደው እንዲያድሩ፣ ጥር 11 ስርዓተ ጥምቀት እንዲፈጸም የተደነገገው ደግሞ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ነው። በዚህ ቀኖና መሰረትም ከጥንት እስከ ዛሬ ታቦታት በእልፍ ምዕመናን ታጅበው ከመንበረ ክብራቸው በመውጣት በባሕረ ጥምቀት ስፍራ ድንኳናቸው ስር ያድራሉ። በሁለተኛው ቀን ዳግም ወደመንበራቸው ይመለሳሉ። ይህ የሚሆነውም በካህናት ስብሐተ እግዚአብሔር፣ በመዘምራን ዝማሬ፣ በእናቶች እልልታ፣ በወንዶቹ ሆታ ነው። በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ20 ሺህ በላይ አብያተ ክርስቲያናትም በየአካባቢያቸው ባሉት አብርሕተ ምጥማቃት (ባሕረ ጥምቀቶች) በዚህ ዑደት ያከብራሉ።

እንደ ጎንደር፣ አክሱም፣ ምንጃርና ላልይበላ እጅግ ለብዙ ዘመናት በተለየ ድምቀትና ሁነት ቢከበርም በሁሉም አካባቢዎች ስርዓተ ጥምቀት ክዋኔ ሲከወን አገርም በውበት አብራ ትጠመቃለች። ዛሬ ላይ ደግሞ ከተመሰረተች 130 በላይ ዓመታትን ያስቆጠረችው አዲስ አበባም በጥምቀት ከሚያብቡ ከተሞች አንዷ ሆናለች። የአዲስ አበባ ጥምቀት በጃንሜዳ ተጀመረ። (ጃንሜዳ ‘ጃንሆይ ሜዳ’ን ይተካል። በአፄ ሠርጸድንግል የተጀመረው ‘ጃን ሆይ’ የሚለው አጠራር ‘ንጉስ ሆይ’ ማለት ሲሆን ጃን የሚለው ቃልም ‘ጃኖ’ ከተሰኘው የነገስታትና መኳንንቱ ልብስ የመጣ መሆኑን ይነገራል)።

ፀሀፊ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ እንደዘገቡት፤ እነእቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ ወደአዲስ አበባ በወረዱ በአራተኛው ዓመት በ1883 ዓ.ም ጥምቀት በጃንሜዳ ተከበረ። በወቅቱ ስምንት ሺህ ህዝብ እንደነበራት የሚነገርላት እንጦጦ (ሀሙስ ገበያ) ባሕረ ጥምቀትን አዲስ አበባ ቀማቻት። በአዲስ አበባ የመጀመሪያው ባሕረ ጥምቀት ሲከበር እንጦጦ ደብረ ፀሃይ ማርያምና ጎረቤቷ ደብረ ሃይል ራጉኤል ታቦታት የከተራ ዕለት ከእንጦጦ ወደጃንሜዳ ወርደው በድንኳን አድረዋል።

እቴጌ ጣይቱና አጼ ምኒልክ በተገኙበት ጥር 11 በጃንሜዳ አዲስ አበባ ጥምቀትን አከበረች። ታቦተ ሕግጋቱ ወደ መንበረ ክብራቸው እስኪመለሱ ድረስ እቴጌ ጣይቱ ምሳ ሳይቀምሱ ቆይተው መድረሱ ሲታወቅ ምልክት የሚሆን ተኩስ ተተኩሶላቸው ነበር አፋቸውን የሻሩት። ለአንድ ዓመት ብቻ ወደ ጃንሜዳ የወረዱት ሁለቱ ታቦታት ግን ባሕረ ጥምቀታቸው እንጦጦ ላይ እንዲያከብሩ ዳግማዊ ምኒልክ በማዘዛቸው ድጋሚ ጃንሜዳ አልወረዱም።

ጃንሜዳ ታሪካዊ ስፍራ ነው። መኪናም ሆነ የመኪና መንገድ ባልነበረበት ዘመን ከክፍለ አገር ወደ አዲስ አበባ የሚጎርፉ መኳንንት ግብር፣ ስንቅ፣ ጦር ወይም ማንኛውንም ጓዝ ለማድረስ በአጋሰስ ስለሚንቀሳቀሱ ከብቶቻቸው ሳር የሚግጡት ጃንሜዳ ነበር። የመኳንንቱ ጦር ሰልፍ የሚያሳይበት፣ ልጅ እያሱን ጨምሮ ልዑላንና ባለሟሎቻቸው ጉግስ የሚጫወቱት፣ ፍርድ የሚፈረድበት፣ ሹማምንት የሚሾሙና የሚሻሩበት፣ ትልልቅ በዓላት የሚከበሩበት በጃንሜዳ ነበር።

አዋጅ የሚነገርበት፣ ታላላቅ ለቅሶ የሚለቀስበት ከዚሁ ሜዳ ነበር። ጃንሜዳ ከዳግማዊ ምኒልክ እስከ መንግስቱ ሃይለማርያም አስተዳድር የጦር ትርዒት ቀርቦበታል። ዛሬ ግን ከሁሉም ሁነቶች በብቸኝነት የሚከወንበት ስርዓት ደማቁ የጥምቀት በዓል ብቻ ይመስላል። ዘንድሮም በነጫጭ አልባሳት በተዋቡ ምዕመናንና ነጫጭ እንግዶች በበዙበት ሁነት ጃንሜዳ ላይ ለ129ኛ ጊዜ ጥምቀት ተከብሯል።

ምንም ዘመኑ ቢዘምን አገርኛ አለባበስ፣ አገርኛ ዝማሬ፣ አገርኛ ትውፊት፣ አገርኛ ጨዋታ፣ አገርኛ ቀለም በጥምቀት በዓል በተግባር ይታያል። ‘አገር፣ ቀለም፣ ዘመን’ እንደሸማው በድርና ማግነት ይተሳሰራሉ። ይህ ትዕይንት ያስደመማቸው ከየዓለም ማዕዘናቱ የጎረፉ ጎብኚዎች አግራሞትና መደነቃቸው ላቅ ያለ ነበር። ኢትዮጵያ በነጻነት ሉዓላዊነቷ ሳይደፈር ዘመን መሻገሯ ቀለሟ ሳይደበዘዝ፣ ትውፊቷ ሳይበረዝ የዘመናት ድልድይ መሻገሯን መስክረዋል።

ከውጭ የመጡት የሩቅ አገር እንግዶች ይህን ይመስክሩ እንጂ ማኅበራዊ እሴቱ የጎላውን ባሕረ ጥምቀት ድባብ የሚያደበዝዙ፣ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊቶች መታየታቸው አልቀረም። ፖለቲካና ሃይማኖት የተዘባረቁባቸው ሰዎች የክፋት ድርጊቶችን የበዓሉን የሐሴት ስሜት ለመበረዝ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በገሃድ ሙከራ ተደርጓል። ይህም በፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ገለጻ፤ ድርጊቱ ‘መርገምትም፤ ክህደትም’ ነበር።

ጥር ወር ከጥምቀት በተጨማሪ ቃና ዘገሊላን ጨምሮ አብዛኛው ቀናት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታቦታት የንግስ ወቅት በመሆኑ በተለይ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ እሴቶች የሚስተዋሉበት ወርም ነው።

የወርኅ ጥር ሌላው ገጽታ ሰርግ ነው። ወላጆች የልጆቻቸውን አዱኛ የሚያዩበት፣ ልጆች እንደ ንጉሥና እቴጌ ተከብረው የሚታዩበትና የሕይወት መስመር የሚጀምሩበት ሰሞን ነው። በተለይም የጥር ወር መጨረሻ አካባቢ ከገጠር እስከ ከተማ ጋብቻ ይፈጸማል። ሰርግና ጋብቻ መብዛቱም ይመስላል ወርሃ ጥርን ‘ዘመነ መርዓዊ’ ያሰኘው። በሰርግ ወቅት የመረዳዳትና አብሮነት እሴት፣ የአገረኛ ቱባ የአጨዋወትና የክዋኔ ጥበባት በተግባር ይታያል።

በነባሩ ባህል ሙሽራን አቋርጦ ማለፍ ነውር ነው፤ ያም ብቻ ሳይሆን ሙሽራይቱንም ማየት የሚችለው ሚዜ ብቻ ነው (አማቷም ብትሆን)። ልደታቸው ጥር ስድስት የሆነው መይሳው ካሳ ወይም ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስም አንድ ወቅት አባ ታጠቅን (ፈረሳቸው) ጋልበው ሲሄዱ መንገድ ላይ ሙሽራ አጋጥሟቸው ከፈረስ ወርደው እጅ ይነሳሉ። ከባለሟሎቻቸው አንዱ ትዕቢተኛ “እርስዎ ንጉስ ሆነው ምነው ለገበሬ ልጅ እጅ ይነሳሉ” ቢላቸው “እኛ ሁልጊዜ ክብር እናገኛለን፤ ሙሽሮች ለአንድ ቀን ይህን ክብር ቢያገኙ ምን ክፋት አለው” በማለት የጋብቻን ታላቅነት መመስከራቸው ይነገራል።

በርግጥ በኢትዮጵያ ጋብቻን አንስቶ ካለአቻ ጋብቻን መዝለል ተገቢ አይደለም። ካላቻ-ጋብቻ አሁን አሁን እየቀነሰ ቢመጣም ግን አልቆመመም። ስለዚህ የወርሃ ጥር ሠርግ ለብዙኀኑ የተድላና ፍስሐ ወቅት ይሁን እንጂ ለታዳጊዎች ደግሞ የሕይወት ጠባሳ ጥሎ አላፊ ወር ነው። አላቻ ጋብቻ የነገስታቱ ልጆችንም አልታገሰም። ለምሳሌ ወሩ ከጥር ቀደም ቢልም የሰርግ ስርዓቱ ተመሳሰይ ስለሆነ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክን ጋብቻ ማንሳት ይቻላል።

ወቅቱ 1873 እንደባተ ነው። በሸዋው ንጉስ ምኒልክ ሃይለመለኮትና ከወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ አራተኛ መካከል የዘውድ ነገር ጥርጣሬ መፍጠሩ አልቀረም። የተረጋጋ መንግስት ለመመስረትና መተማመን ለመፍጠር ‘ልጅህን ለልጄ’ መባባል ነባር ወግ ነው። ከወረኢሉ ባላባት ከወይዘሮ አብቺው በያን የምትወለደው የስድስት አመቷ ህጻን ዘውዲቱ ምኒልክ ለዘውዱ ማረጋጊያ ለራስ አርዓያ ዮሐንስ ታጨች። ምኒልክ ልጅቷ ለአቅመ ጋብቻ አልበቃችም ቢሉም ዮሐንስ ግን ‘የንጉስ ልጅ በአንቀልባም ቢሆን ትሄድ አይደለምን’ በሚል ጋብቻው ተቆረጠ።  ሰርጉም እንጦጦ ሳይሆን ምኒልክ ከመሰረቷትና ከሚወዷት ከተማ ወረኢሉ ነበር። የሰርግ ዳሱ ተጣለ፤ ግምጃው ተነጠፈ፤ ድግሱ ተዘጋጀ፤ ሰራዊቱም በወርቀ ዘቦ ቀሚስተጌጠ።

በዕለቱ (የጥቅምት ሚካኤል ዕሁድ ዕለት) ሙሽራው ራስ አርዓያ ሰራዊቱ ተሰልፎ ተቀብሎት ወረኢሊ ገባ። ድልብ ሰንጋ ከነአረቂው ግብር ገባ፤ ተበላ፤ ተጠጣ። ሰርጉን የታደሙት ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ለሙሽራው ለራስ አርዓያ የተበረከተውን ሽልማት ሲግልጹ “ባለወርቅ መጣብር ፈረስና በቅሎ፣ የወርቅ ጋሻ፣ የወርቅ ጎራዴ፣ የወርቅ ቢተዋ፣ ልዩ ልዩ ቀሚሶች፣ ሁለት ማለፊያ ለምዶች፤ ግምጃ ሱሪ፣ ግምጃ መታጠቂያ፣ ድርብ ግምጃ፣ ጥላ፣ አንድ መድፍ፣ 500 ነፍጥ፣ 500 በቅሎና ፈረስ፣ 500 አገልጋይ፣ 100 ሰርፍና ስጋጃ ምንጣፍ፣ ግራ ቀኝ የወርቅ መከዳ፣ የብር ታዳን ሰሃን፣ 200 ብርሌና ብርጭቆ፣ 5 ሺህ ላምና በሬ፣ 5 ሺህ በግና ፍየል፣ 5 ሺህ ጥሬ ብር፣ አንድ ግምጃ ድንኳን፣ 30 ለምድ፣ 100 ቀጭን ኩታና ስድስት መቶ ኩታ ነው” ይላሉ።

ይህ ለሙሽራው ብቻ ሲሆን ለሙሽራው ሚዜ መኳንንት ደግሞ ሁሉም በየራሳቸው ተሸልመዋል። ሲዘፈንና ሲሸለም ውሎ አድሮ በነጋታው ሰኞውን ሙሽሪት ዘውዲቱ ተነሳች። 12 መድፍ ተተኮሰ። ወረኢሉም በመድፍና በሌላ ነፍጥ ጢስ ተሸፈነች። ሙሽራዋ በአራት ማዕዘን በወርቅና በብር ድባብ ተደብቦላት (ተዘርግቶላት)፣ ደንገጡሮች ከኋላና ከፊት በወርቅ አልባሳት አጊጠው፣ መኳንንቱና ሰራዊቱ እየዘፈኑ ተሸኘች።

እንዲህ ‘አጃይብ’ በተባለለት የሠርግ ስነ ስርዓት የተዳረችው የኋላዋ ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ራስ አርዓያ ረጅም ዕድሜ ሳይቆይ ሞተባት። ለሁለተኛ ጊዜ ለደጃች ውቤ አጥናፍ ሰገድ ብትዳርም አለመደችም፤ አንድ ቀን ከባለቤቷ ጋር ተጋጭታ ከውቤ በርሃ እያለቀሰች አራት ኪሎ እንደገባች ተፋታ ቀረች። ለሶስተኛ ጊዜ ለእቴጌ ጣይቱ ወንድም ልጅ ለራስ ጉግሳ ወሌ ተዳረች።

ወይዘሮ ዘውዲቱ ልጅ እያሱ ከመንበረ ስልጣን ከወረደ በኋላ ንግስና ብትቀባም ከራስ ጉግሳ ወሌ ጋር የፈጸመችው ትዳሯ ግን ሳይሰምር፤ ልጅም ሳታፈራ በድንገት አረፈች። በስድስት ዓመቷ እንደተዳረችው የኋላዋ ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ምኒልክ አይነት ስንቶች ከመኳንንት እስከ ተራ ገበሬ ልጆች ካለዕድሜያቸው ተድረው አካላዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ እንዳጋጠማቸው፣ ቀጣይ የሕይወት መስመራቸው እንደተበላሸባቸው ቤት ይቁጠረው። መልካም ወርኃ-ጥር!!

የመምህር ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር ‘ሕብረ ብዕር’፣ የፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ወልደአረጋይ ‘ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ’ እና ሌሎች ፅሁፎች ለዚህ ጸሁፍ ግብዓትነት አገልግለዋል።