የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከነገ በስቲያ ከዩጋንዳ አቻው ጋር የማጣሪያ ጨዋታ ያደርጋል

494

አዲስ አበባ ጥር 15/ 2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የፊፋ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ከነገ በስቲያ ከዩጋንዳ አቻው ጋር በባህርዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲየም ያደርጋል።
ህንድ በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም በምታስተናግደው ሰባተኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታ ከሁለት ሳምንት በፊት መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም በካምፓላ ስታርስ ታይምስ ስታዲየም አድርጎ በዩጋንዳ አቻው 2 ለ 0 መሸነፉ አይዘነጋም።

በአሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ የመልስ ጨዋታውን ከነገ በስቲያ በ10 ሰዓት ለማድረግ ከዩጋንዳ ከተመለሰ በኋላ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዝግጅት ሲያድርግ ቆይቷል።

ከሜዳው ውጪ ሽንፈት በማስተናገድ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ የቤት ስራው ከባድ የሆነበት ብሔራዊ ቡድኑ፤ ሶስትና ከሶስት በላይ የጎል ልዩነት ማሸነፍ ብቻ ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፈዋል።

በአሰልጣኝ አዩባ ከሊፋ የሚሰለጥነው የዩጋንዳ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን 27 ልዑካን ይዞ ዛሬ ረፋዱ ላይ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ቡድኑ ጨዋታው ወደ ሚደረግበት ባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚያቀና ይሆናል።

በሜዳው ብሔራዊ ቡድኑ ያስመዘገበው ድል የማለፍ እድሉንም ሰፊ አድርጎታል።

አፍሪካ በዓለም ዋንጫው ሁለት ብሔራዊ ቡድኖችን የማሳተፍ ኮታ አላት።

በህንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 7ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ 16 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።

በሌላ የእግር ኳስ ዜና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

ነገ በስታዲየም ግንባታ ምክንያት ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታዲየም እያደረገ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም በትግራይ ስታዲየም ስሑል ሽረ ከጅማ አባ ጅፋር በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህርዳር ከተማን ያስተናግዳል።

በክልል ከተሞች ወላይታ ድቻ በሜዳው ከሊጉ መሪ መቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከሲዳማ ቡና፣ በትግራይ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ይጫወታሉ።

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም በዝዋይ ሼር ሜዳ ወልቂጤ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በተመሳሳይ ከቀኑ 9 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወልቂጤ ከተማ በስታዲየም እድሳት እንዲሁም ሰበታ ከተማ በስታዲየም ግንባታ ምክንያት ጨዋታቸውን በሌላ ሜዳ እያደረጉ የሚገኙ ክለቦች ናቸው።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ19 ነጥብ ነጥብ ሲመራ፣ ፋሲል ከነማና ስሑል ሽረ በተመሳሳይ 15 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል።

አዳማ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በዘጠኝ ግቦች ሲመራ፣ የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤልና የባህርዳር ከተማው ፍጹም አለሙ በተመሳሳይ ስድስት ግቦች ይከተላሉ።