የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ

70
ጥር 15 / 2012 (ኢዜአ) የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻው የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን እሁድና ሰኞ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ። ከነገ በስቲያ ሶዶ ላይ ከቀኑ በ8 ሠዓት ወላይታ ድቻ የፕሪሚየር ሊጉን መሪ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲን የሚያስተናግድበት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። ወላይታ ድቻ ባለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ ሲሆን መደወላቡ ዩኒቨርሲቲን በአንድ ነጥብ በልጦ እንደነበር የሚታወስ ነው። በ14 ነጥብ ሊጉን የሚመራው መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ13 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል። ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በፕሪሚየር ሊጉ በሁለተኛ ደረጃ ከሚገኘው ሙገር ሲሚንቶ ጋር ከጠዋቱ 3 ሠዓት ከ30 ይጫወታል። ከቀኑ በ8 ሠዓት ደግሞ መከላከያ ከጣና ባህርዳር ጫወታቸውን ያካሂዳሉ። ሰኞ ጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሠዓት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም አዲስ አበባ ፖሊስና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በአራተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ሶዶ ላይ መካሄድ የነበረበትና ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመው የወላይታ ድቻና መከላከያ ተስተካካይ ጨዋታም በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል። ከሁለቱ ክለቦች ውጪ የተቀሩት ክለቦች የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብራቸውን በዚህ ሳምንት በሚደረጉ ጨዋታዎች እንደሚያጠናቅቁ ከኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በሌላ ዜና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከጠዋቱ 3 ሠዓት፣ ፌዴራል ፖሊስ ከቡታጅራ ከተማ ከረፋዱ 4 ሠዓት ከ30 እና መከላከያ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከረፋዱ 5 ሠዓት ከ30 ይጫወታሉ። ከነገ በስቲያ ሚዛን አማን ላይ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማን ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከጎንደር ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ በ3 ሠዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። በወንዶች በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የካ ክፍለ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ30፣ ውቅሮ ላይ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ አጋዚ ውቅሮ ከሀዋሳ ከተማ ከጠዋቱ በሶስት ሠዓት ይጫወታሉ። በሴቶች ባህርዳር ላይ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ከጎንደር ከተማ፣ ጅማ ላይ ጅማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሶስት ሠዓት የሚጫወቱ ይሆናል። በወንዶች ጎንደር ከተማ፣ በሴቶች የካ ክፍለ ከተማና ወልቂጤ ከተማ በሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታ የማያደርጉ አራፊ ክለቦች ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም