በደቡብ ክልል ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

67
ሀዋሳ ጥር 15 /  2012 (ኢዜአ)  በደቡብ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ። ባለስልጣኑ ከ1 ሺህ የሚበልጡ ግበር ከፋዮች ኦዲት በማድረግ 210 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘይቱና ኢብራሂም በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት በሰባት በመቶ ብልጫ አሳይቷል። ገቢው ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤቶች እንደተሰበሰበም አስረድተዋል። በበጀት ዓመቱ 12 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የክልሉን ወጪ 30 በመቶ በራስ አቅም ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንም ወይዘሮ ዘይቱና ተናግረዋል። በክልሉ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በገቢ አሰባሰብ ሂደት ላይ  አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮ እንደነበር አመስታውሰው፤በተያዘው ዓመት በክልሉ ከሸካ ዞን በስተቀር በሌሎቹ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል። በግማሽ ዓመቱ 17 ሺህ የሚጠጉ ግብር ከፋዮችን ወደ ታክስ ሥርዓቱ መግባታቸውን ዋና ዳይሬክተሯ አመልክተዋል። የንግዱ ኅብረተሰብ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን አጠቃቀም ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ በተደረገው ጥረት 700 አዲስ ነጋዴዎች ማሽኑን መጠቀማቸውን አስታውቀዋል። ባለስልጣኑ በ1ሺህ239 ግብር ከፋዮች ላይ ባደረገው የኦዲት  ከ210 ሚሊዮን ብር በላይ ግኝት መሰብሰቡን ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም