ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንትና የንግድ መዳረሻ ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

114
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻና አዋጭ የንግድ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ ። በስዊዘርላንድ ዳቮስ የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ "ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና" በሚል ርዕስ የፖናል ውይይት ተካሄዷል። በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል ። ''ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንትና የንግድ መዳረሻ ለማድረግ በመንግሥት የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ'' ብለዋል። በአገሪቱ ያለውን የኢንቨስትመንት ነባራዊ ሁኔታ ለዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎች የበለጠ ጋባዥ ለማድረግ በርካታ የህግ ማሻሻያዎችና የማትጊያ ማዕቀፎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል። የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጎልበት የሚስተዋሉ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታትና አስቻይ ሁኔታዎችን ለማጠናከር መንግሥት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ያሉት ዕምቅ ተፈጥሯዊ ፀጋዎችና የኢንቨስትመንት ዕድሎች ሰፊ በመሆናቸው ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በዘርፉ እንዲሳተፉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ የሚደመጡት አዎንታዊ መረጃዎች ለቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት አጋዥ መሆናቸውን በአድናቆት ገልፀዋል። በውይይቱ ላይ የተለያዩ የኩባንያ መሪዎች 'የኢንቨስትመንት ዘርፉ ፈተናዎች ናቸው' ብለው ላነሷቸው ጥያቄዎች በተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ምላሽ እንደተሰጠባቸው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም