በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ የታየውን ለውጥ አብሮነትን ለማጠናከር ሊያገለግል ይገባል …የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን

101
ሀዋሳ ጥር 14/2012  ኢዜአ በያዝነው ዓመት በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ የታየውን አበረታች ለውጥ ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የውድድር ሥፍራዎች የሠላምና አብሮነት መድረኮች እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ተመለከተ። የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ያለፉትን ስድስት ወራት አፈፃፀምና የዘርፉን የ10 ዓመታት መሪ ዕቅድ የተመለከተ ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ነው። በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር እንዳሉት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በውድድሮች ላይ የታዩ ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደላቸው ተግባራት በሀገሪቱ ስፖርት ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል። “በዚህም የንብረት ውድመትና የአካል ጉዳትም ተከስቷል” ብለዋል። እነዚህን ክስተቶች ለማስቀረት የሊግ ኮሚቴ፣ የእግር ኳስ ክለብ ደጋፊ ማህበራት፣ የፀጥታ አካላትና መገናኛ ብዙሃን ባደረጉት ርብርብም በዘርፉ አበረታች ውጤት ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ። በግማሽ ዓመቱ መንግስታዊና ህዝባዊ የስፖርት አደረጃጀቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ህዝባዊ መሠረታቸው እንዲሰፋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንን ገለልጸው ከዓመታት በፊት ተቋርጦ የነበረው የብሔራዊ ስፖርት ምክር ቤት ዳግም መመሥረቱንም አስረድተዋል። በስፖርቱ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበት አዲስ ሀገራዊ የስፖርት ልማት ሪፎርም ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ሰነዱ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ወርዶ ውይይት እየተካሄደበት እንደሚገኝ ተናግረዋል። የሪፎርም ፕሮግራሙ የዘርፉ የቀጣይ 10 ዓመታት መሪ ዕቅድ አካል መሆኑንም ነው የጠቆሙት። በኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ በበኩላቸው ስፖርትን ለልማት መሳሪያነት የተጠቀሙ ሀገሮች ዘርፉን ከማስፋት በሻገር ለሠላም፣ አንድነት፣ ብልፅግና እንዲሁም ለሀገራዊ ኩራት ምንጭነት ይጠቀሙበታል። በሀገራችን ስፖርትን ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚፈለገው ልክ ሥራ ላይ እንዲውል አለመደረጉንም ጠቁመዋል። “የኢፌዴሪ ስፖርት ፖሊሲ ተቀርፆ ሥራ ላይ በዋለባቸው ሁለት አስርት ዓመታት የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች ቢኖሩም ስፖርቱ ከዕድሜው አኳያ በሚፈለገው ልክ አላደገም” ብለዋል። በመንግስት ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በርካታ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል። የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ የሺዋስ አለሙ በበኩላቸው ክልሉ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኑ ስፖርታዊ ውድድሮችን እንደመልካም አጋጣሚ ወስዶ መስራት ከተቻለ በሰላም፣ ልማትና አንድነት ላይ የሚያሳድሩት አወንታዊ እገዛ ከፍተኛ ነው ብለዋል። ይህንን በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር ካልተቻለም በተቃራኒው አሉታዊ ጫናቸው የበዛ እንደሚሆን ገልፀዋል። ስፖርታዊ ጨዋነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ የሺዋስ የውድድር ዘመኑ ከመጀመሩ አስቀድሞ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ በሊጎች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች አመራሮች እንዲሁም የደጋፊ ማህበራት ተወካዮች በጉዳዩ ላይ በመምከር ከስምምነት ላይ ደርሰው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስረድተዋል። ዘንድሮ እስከ አሁንም የክልሉ ክለቦች ባደረጓቸው ውድድሮች ላይ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል አለመታየቱንም ገልጸዋል። ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ከኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፣ ከፌዴራል ፣ ከክልልና ከተማ አስተዳደር ኮሚሽኖች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ አመራሮችና ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም