ቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት በማድረስ ዓላማን ለማስፈጸም መሞከር የኋላቀርነትና የደካማ አስተሳስብ መገለጫ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

72
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 14/2012 የኃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት በማድረስ ዓላማን ለማስፈጸም መሞከር የኋላቀርነትና የደካማ አስተሳስብ መገለጫ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ቤተ እምነቶችን በማቃጠል ማንንም ማሸነፍ እንደማይቻልም ጨምረው ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ከተወጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ ታዳሚዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው። ተሳታፊዎቹ በውይይቱ አሉብን ያሏቸውን ችግሮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተውላቸዋል። ተሳታፊዎቹ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነባሩን የዜጎች እሴት በጣሰ መልኩ በቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት እተፈጸመ መሆኑን ነው ያነሱት። የተለያየ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ግለሰቦች ጥቃቱን ከማቀነባበር ጀምሮ ወደለየለት የኃይማኖት ግጭት ለመውሰድ በስፋት እየተሳተፉ መሆኑን በመጥቀስ። መንግስት የኃይማኖት ተቋማትን ለፖለቲካ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ የሚጠቀሙ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድም ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው "እኛ ኢትዮጵያውያን ረዥም ዘመናትን የተሻገረ የመከባበር እሴት ያለን ህዝቦች ነን" ሲሉ ነው የተናገሩት። ይህን እሴት ጠብቆ ለትውልድ ማሸጋገር ደግሞ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን በመግለፅ። ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ ቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት ማድረስ ግን ዋነኛው "የኃላቀርነትና የደካማ አስተሳሰብ መገለጫ ነው" ብለዋል። "ኦርቶዶክስም ሆነ እስልምና ሀገር ናቸው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ከንቱ ልፋት እንጂ ቤተ ክርስቲያንና መስጂድ በማቃጠል የምናሸንፈውም ሆነ የምናጠፋው ሃይል አይኖርም" ብለዋል። ክርስቲያኑ በየአካባቢው ላሉ ለመስጊዶች፤ ሙስሊሙ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኖች ዘብ መቆም እንዳለበትም ጥሪ አሳስበዋል። ዜጎች የተለያዩ እኩይ ዓላማ ያሏቸው ግለሰቦች በሚያመጧቸው አጀንዳዎች እንዳይታለሉም መክረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም