በደቡብ ክልል የሚነሱ አስተዳደራዊ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚሰራ ኮሚቴ አዋቅረናል… ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

601

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 14/2012 በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚነሱ አስተዳደራዊ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚሰራ ኮሚቴ መዋቀሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይፋ አደረጉ።
ኮሚቴው በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ዞኖች የተወከሉ ግለሰቦችን ያካተተ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዛሬ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ከተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።

መድረኩ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ‘የክልልነት ጥያቄ’ በሚል መነሻ በክልሉ የሚፈጠሩ ያልተገቡ እንቅስቃሴዎችን በውይይት መፍታትን ዓላማው አድርጎ መዘጋጀቱ ነው የተገለጸው።

በክልሉ በቀጣይ ሊፈጠሩ ለሚችሉ ችግሮች አሳታፊ መፍትሄዎችን ማበጀትም ሌላው የውይይቱ አጀንዳ ነው።

የውይይቱ ተሳተፊዎች እንደመጡበት አካባቢ ተጨባጭ ሁኔታ ‘በልዩ ወረዳ መዋቀር አለብን’ ከሚል ሃሳብ ጀምሮ ‘ራሳችንን ችለን በክልል እንደራጅ’ የሚሉ ጥያቄዎችንም አንስተዋል።

‘አሁን ያለው መዋቅር ያሉብንን የልማት ጥያቄዎች በእኩልነት መፍታት አይችልም’ የሚለውን ሃሳብ ደግሞ ለጥያቄያቸው በምክንያትነት አቅርበዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ‘እኛ የደቡብ ሕዝቦች ተመሳሳይ አኗኗርና ስነ-ልቦና ያለን በመሆናችን ከምንለያይ ይልቅ አንድነት ይሻለናል፤ የክልልነቱ ጥያቄ አይጠቅመንም’ የሚል አስተያየትም ከተሳታፊዎች ተነስቷል።

በተጨማሪም የመንገድ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የሆስፒታል፣ የኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉላቸውም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በምላሻቸው መንግስት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የዜጎችን አንገብጋቢ ጥያቄዎች መመለስ ቁልፍ ስራው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ዜጎች ችግር ተንታኞች ብቻ ሳይሆኑ ለችግሮች የመፍትሄ ቁልፍ መሆን አለባቸው ነው ያሉት።

የተነሱ አስተዳደራዊ የአደረጃጀት ጥያቄዎችም በእልህ ሳይሆን በሰከነ ውይይት ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ለመፍታት ከክልሉ ሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ግለሰቦች ያሉበት ኮሚቴ መዋቀሩን ጠቁመው፤ ኮሚቴው በቀጣይ ሕዝቡን በማወያየት የመፍትሄ አቅጣጫ ነው ያለውን ሃሳብ ይዞ እንደሚመጣ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ለመንገድ መሰረተ ልማት 48 ቢሊዮን ብር ተበጅቶ በተለይ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር አብይ ገልጸዋል።

ይህም ክልሉን በስፋት ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ነው የጠቆሙት።

የጤና ሚኒስቴር አዲስ ባዘጋጀው የጤና ሪፎርም የግብዓት እጥረት ያሉባቸውን ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት ለሟሟላት በልዩ ትኩረት ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል።

ነገር ግን መንግስት በአጭር ጊዜ ዕቅዱ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ዩኒቨርሲቲዎችን እንደማይገነባና ነባሮች ይበልጥ እንዲጠናከሩ እንደሚሰራ ገልጸዋል።