የአገር ሽማግሌዎች ወጣቱን ለአገር ግንባታ እንዲያንቀሳቅሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠየቁ

58
ጎንደር ጥር 14 / 2012 (ኢዜአ)  ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የሚሰሩ የአገር ሽማግሌዎች ወጣቱን ለጠንካራ አገር ግንባታ እንዲያንቀሳቅሱ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጠየቁ። በጎንደር የጥምቀትን በዓል  ለታደሙት የጋሞ አባቶች ሽኝት ተደርጎላቸዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም በሽኝቱ ወቅት እንዳሉት  ሃይማኖትና ብሄርን ሳይወክሉ  የሚንቀሳቀሱት የአገር ሽማግሌዎች ወጣቱ  አንድነቷና ሰላሟን የተጠበቀች አገር እንዲኖረው ምክር መስጠት አለባቸው። በየአካባቢው ለአገር አንድነትና ለሕዝቦቿ ሰላም አብዝተው የሚጨነቁና ችግር ፈች የአገር ሽማግሌዎች እንደሚገኙ አውስተው፣በልምድ ያካባቷቸውን የችግር አፈታት መንገዶች በማሳደግም ወጣቱን ማስተማርና መምከር ይገባቸዋል ብለዋል። የአገር ሽማግሌዎቹ ኅብረት በመፍጠርም ተሞክሯቸውን በመለዋወጥ በአገር ግንባታና ሰላምን በማስፈን እያደረጉ ያሉትን አስተዋፅኦ ማጠናከር እንደሚኖርባቸውም አብራርተዋል። የጎንደር ሰላምና ልማት ሸንጎ ሰብሳቢ አቶ ባዩ በዛብህ እንዳመለከቱት የጋሞ አይነት አባቶች ልምድን በማስፋት በመላ ኢትዮጵያ ቁጥራቸውን ማሳደግ ይገባል፡፡ የጋሞ ወጣቶች የአባቶችን ልመናና ፍቅር ወዳድነት በመስማት ስሜታቸውን ተቆጣጥረው ከህገ-ወጥ ድርጊት መታቀባቸውም ወጣቶቹ ያላቸውን ኢትዮጵያዊ ስነ-ምግባርና ፅናት እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የእኛም የእናንተም አባቶች ትግል ኢትዮጵያን ለዛሬ እንድትደርስ አድርጓል፤›› ያሉት አቶ ባዩ፣ አሁንም አገሪቱ የተጋረጣባትን አደጋ በጋራ ተባብሮ መፍታት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ከሁለም አካባቢ ካሉ የአገር ሽማግሌዎች ‹‹እንደ አንድ አንደበት ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ›› ሆነው በመስራታቸው ለአገር የሚበቃ ተሞክሮ ማስገኘት መቻላቸው ያኮራል ብለዋል። ከጋሞ አባቶች መካከል አቶ ካዎ ታደሰ በበኩላቸው በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና አንድነት ለማምጣት በየትኛውም አቅጣጫ ያለ ኢትዮጵያዊ በጋራ መስራትና መስዋዕትነት መክፈል ይገባል በማለትም ተናግረዋል፡፡ ''ለበጎነታችን በተቃራኒው የቆመ ጠላት አይጠፋም'' ያሉት አቶ ካዎ፣ በኢትዮጵያዊ ስነ ልቦናና ባህል ግን ጠላትን ማሸነፍ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ መገፋፋት መተላለቅን እንደሚያመጣ መገንዘብ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ መቀራረብና በጋራ መስራት ወደፊት ሊመጣ ከሚችል ችግር ሁሉ ይታደጋል ብለዋል። የሰላምን ኃሳብ ማፍለቅ ብቻ ሳይሆን፤ ማሳደግና ዳር ማድረስ ያስፈልጋል ያለው ደግሞ ከጋሞ የሰላም ተጓዦች ወጣት ደጉ ደሳለኝ ነው፡፡ ሁሉም ወጣት ኢትዮጵያዊነትን በመስበክ ከአባቶቻቸው የተረከቧትን አገር ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ  እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎንደር ከተማ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተሳትፈዋል። የጎንደር ከተማና የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች በጋራ የሚሰሩበትን የቃል ኪዳን ሰነድም ተፈራርመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም