በአገሪቷ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሰላማዊ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ ነን-ግንባሩ

99
አዲስ አበባ ሰኔ18/2010 በአገሪቷ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሠላማዊ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀቱን የኦሮሞ አንድነት ነጻነት ግንባር አስታወቀ። ዘጠኝ አባላት ያሉት የድርጅቱ ልዑክ ዛሬ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የመንግሥት ከሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ አቀባበል አድርገውለታል። የልዑካን ቡድኑ ከአሜሪካ፣ ካናዳና አውሮፓ አገራት የተውጣጡ ሲሆን በቀጣይ በምን መልኩ እንደሚሳተፉ ለመወያየት መምጣቱ ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። በዚሁ መሰረትም የኦሮሞ አንድነት ነጻነት ግንባር ጥሪውን ተቀብሎ አዲስ አበባ ገብቷል። የልዑካን ቡድኑ መሪ አቶ ተማም ባቲ "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቷ እየታየ ያለው ለውጥ ወደ አገር ቤት ተመልሰን እንድንገባ አነሳስቶናል" ብለዋል። በትጥቅም በሠላማዊ መንገድም የሚታጋሉ ተቃዋሚዎችን መጋበዝ የሚያበረታታ ነው፤ እውነተኛ ጥሪ ነውም" ብለዋል። ለውጡ እውነተኛ ለውጥ ነው ያሉት አስተባባሪው፤ "ቀሪውን አብሮ መሙላት እንችላለን፤ ለውጥ ምን ጊዜም ሙሉ አይደለም የሚጎለውን  እድሉ ካለ አብረን ማሟላት እንችላለን በሚል ነው የመጣነው" ሲሉም ጠቁመዋል። ድርጅቱ በሠላማዊ መንገድ የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ እንዲቀጥልም የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጸው፤ ህጋዊ በሆነ መንገድ ተመዝግበን መንቀሳቀስ እንፈልጋል ብለዋል። “መንግሥት የለውጡ አካል ሁኑ፤ ብሎ ላቀረብልን ግብዣም የላቀ ምስጋና ማቅረብ እንሻለን" ነው ያሉት። “አሁን እየታየ ያለው ለውጥ እንዲመጣ ብዙ ሰዎች መስዋዕት ሆነዋል፣ ብዙ ሰዎች ቆስለዋል፣ ብዙ ሰዎች አካል ጎደሎ ሆነዋል'' ሲሉም ተደምጠዋል። ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው ግንባሩ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ የትጥቅ ትግሉን በማቆም ህገ መንግስታዊና ህጋዊ መድረኩን ለመቀላቀል መወሰኑ እንደሚያስመሰግነው ተናግረዋል። ግንባሩ በሰላማዊ መንገድ የሚሳተፉበት መንገድ ለማማቻቸት ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚደረጉም አመልክተዋል። መንግሥት የጀመረው የሰላም ጥሪ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ይህም ለአገሪቷ ሠላም፣ አንድነትና ዲሞክራሲን ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም