የአንበጣ መንጋ በመኸር እርሻ ምርት ላይ የጎላ ጉዳት ሳያስከትል መከላከል ተችሏል

54
ጥር  14/2012 ( ኢዜአ) ባለፉት ወራት በኢትዮጵያ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በአገሪቱ የመኸር እርሻ ምርት ላይ የጎላ ጉዳት ሳያስከትል መከላከል መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። መንግስት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ተግባር ባያከናውን ኖሮ የዘንድሮው የመኸር ምርት ሙሉ በመሉ ይወድም ነበር ብሏል ሚኒስቴሩ ። የአንበጣ መንጋ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል። የሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሳላቶ ከየመንና ከሶማሌላንድ የገባው የአንበጣ መንጋ በአፋርና ሶማሌ ክልል እንዲሁም በጥቂቱ ምስራቅ አማራ አካባቢ ተከስቶ መራባቱን ገልጸዋል። በተለያየ ጊዜ ከጎረቤት አገራት የገባው የአንበጣ መንጋ በሰብል ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ አቅም ነበረውም ብለዋል። ነገር ግን አደጋውን ለመከላከል አስቀድሞ በተደረገው ዝግጅትና ከተከሰተ በኋላም ከህብረተሰቡና ከተለያዩ ተቋማት ጋር የተወሰደው የአንበጣ መንጋ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ የመኸር ምርቱን መሰብሰብ ተችሏል ነው ያሉት። አርሶ አደሩና የግብርና ኤክስቴንሽ ሰራተኞች አደጋውን ከመከላከል ጋር በተያያዘ ሊኖራቸው የሚገባውን ግንዛቤ ለማሳደግና አስፈላጊውን መረጃ  በአግባቡ ለመለዋወጥ የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት ውጤታማ የመከላከል ተግባር መከናወኑን ጠቅሰዋል። የአንበጣ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ህብረተሰቡን ያሳተፈ አፋጣኝ እርምጃ መወሰዱም ውጤታማ አድርጓል፡፡ መንጋው ጉዳት ያደረሰው የመሬት አቀማመጣቸው ለመከላከል አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎችና የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች መሆኑን ጠቁመዋል። በአራት አውሮፕላኖች በመታገዝ የኬሚካል ርጭት የተከናወነ ሲሆን በዚህም ከ200 የሚልቁ የአንበጣ መንጋዎችን መከላከል ተችሏል ብለዋል። በአጠቃላይ በአገሪቱ 65 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መንጋው መከሰቱን በማከል። የአንበጣ መንጋ ስጋቱ አሁንም እንዳለ የሚገልጹት አቶ  ዘብዲዮስ ከሌሎች አገራት በሁለት አቅጣጫ ይገባ የነበረው የአንበጣ መንጋው ወደ አምስት አቅጣጫ አድጓል ብለዋል። ይህንን አደጋም አስቀድሞ ለመከላከልና መረጃ ለመለዋወጥ ከተለያዩ አገራት ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። በዘንድሮ የመኸር እርሻ ለማግኘት ከታቀደው ምርት አብዛኛው መሰብሰቡን ጠቁመዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም