ዓለም አቀፍ የአንድ ትሪሊዮን ዛፍ መርሃ ግብር ይፋ ሆነ።

79
አዲስ አበባ ጥር 14/2012 (ኢዜአ)  የዓለም ምጣኔ ሃብት ጉባዔ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ዓለም አቀፍ የአንድ ትሪሊዮን የዛፍ ችግኞችን ተከላ መርሃ ግብር ይፋ አደረገ። በዳቮስ እየተካሄደ ያለው ጉባዔ ይፋ ያደረገው መርሃ ግብር የዛፍ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ያለመ ነው። መርሃ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ አገራት መሪዎች ቃል ገብተዋል። ከነዚህ መካከል በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ባላቸው አቋም ግርምትን የሚፈጥሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለመርሃ ግብሩ አዎንታዊ ምላሽ አሳይተዋል ተብሏል። በመሆኑም አሜሪካ ከ50 እስከ 100 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞችን ትተክላለች ተብሎ ይጠበቃል። የኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት ኢቫን ዱኩኢ ማርኩዝ የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ፈተና እየሆነ መምጣቱን በአጽንኦት አንስተዋል። የደን ጭፍጨፋን መከላከል ካልተቻለ ውጤታማ ዕድገት ማስመዝገብ እንደማይቻልም ገልጸዋል። እናም ኮሎምቢያ በቀጣዩ ነሐሴ 180 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞችን ለመትከል ማቀዷንና ቁርጠኝነታቸውንም አሳይተዋል። የምስራቅ አፍሪካ የደን ሽፋን እየተመናመነ በመምጣቱ መንግስታት ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል። ከማምረቻ ዘርፍ በሚለቀቅ በካይ ጋዝና በኃይል አጠቃቀም ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የዓለም ስጋት እየሆነም መጥቷል። በካይ ጋዞችን በመልቀቅ ቻይናና አሜሪካ ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በካይ ጋዞችን በመልቀቅ ከአንድ በመቶ በታች አስተዋጽኦ ያላት ኢትዮጵያም በደን ጭፍጨፋና በአካባቢ መራቆት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ገፈት ቀማሽ እየሆነች ነው። ይህን ለመቋቋም መንግስት የአካባቢ ጥበቃና ችግኞችን የመትከል ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም ከ4 ቢሊዮን በላይ የዛፍ ችግኞችን መትከሏ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ዓመትም ተመሳሳይ መርሃ ግብር እንደሚኖር መገለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም