ሞተር ብስክሌቶችና ባጃጆች ለወንጀልና አደጋ መባባስ ምክንያት ሆነዋል…የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች

67

ሁመራ ጥር 14 ቀን 2012  (ኢዜአ) በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በሁመራና አካባቢው የሚቀሳቀሱ ባለ ሁለትና ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ለህገ-ወጥ ንግድና ለትራፊክ አደጋ መባባስ ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውን ተገለጸ፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎችና የሚመለከታቸው ኃላፊዎች እንዳሉት

ኢትዮጵያ ከሱዳን በምትዋሰንበት ድንብር ልዩ ስሙ ዲማ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ዋና የኮንትሮባንድ ማመላለሻ መስመር መሆኑም ተመልክቷል።

ነዋሪነታቸው ዲማ ድንበር ላይ የሆነው አቶ ተወልደ መኮነን እንደተናገሩት በርካታ ባጃጆችና ሞተር ብስክሌቶች በመስመሩ በኩል በህገ-ወጥ ንግድ ላይ ስለሚሳተፉ የተረጋጋ የትራንስፖርት አገልግሎት አይሰጡም።

"ቡናና ጤፍን ጨምሮ ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦችን ከህግ አስከባሪዎች ደብቀው ለማሸሽ በመፈለግ ከመጠን በላይ በፍጥነት ስለሚነዱ ለትራፊክ አደጋ መከሰት መንስኤ እየሆኑ መጥተዋል" ብለዋል።

መነሻቸውን ሁመራ ከተማ በማድረግ ልዩ ስሙ ዲማ ተብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያ ጠረፍ ቦታ ድረስ ባጃጆችና ሞተር ብስክሌቶች በብዛት እንደሚቀሳቀሱ የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ሀይለ ዜናዊ የተባሉ የሚሊሻ አባል ናቸው።

በአንድ ሞቶር ብስክሌት እስከ አራት ሰውና የኮንትሮባንድ እቃዎችን ይዘው በፍጥነት ስለሚጓዙም በመገልበጥ አደጋ መብዛት መስጋታቸውን አስረድተዋል።

ሞተር ብስክሌታቸው ለሶስተኛ ጊዜ የኮንትሮባንድ ንግድ ሲካሔድበት መያዙን የተናገሩት ደግሞ አቶ ኪዳነ ገብረ ማርያም ናቸው።

እንደ እሳቸው ገለጻ ሞተር ብስክሌታቸውን የተከራየው አሽከርካሪ ባልተስማሙበት የህገ-ወጥ ንግድ ላይ ተሰማርቶ በመገኘቱ ንብረታቸው መያዙን አስረድተዋል።

ችግሩ ሌሎችም ላይ እንዳይደርስ ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ለመስራት እንደተዘጋጁም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን የሁመራ ቅርንጫፍ የኮንትሮባንድ ክትትል ባለሞያ አቶ ወንድማገኝ እምብሎ እንደገለጹት በያዝነው ዓመት በኮንትሮባንድ ስራ ተሰማርተው የተገኙ 61 ባጃጆችና ሞተር ብስክሌቶች ተይዘዋል።

ከነዚህ ውስጥም አራቱ ከያዙት ንብረት ጋር ሲወረሱ ሌሎቹ ባለንብረቶቹ የሶስተኛ ወገን ንብረት ናቸው የሚል ምክንያት በመቅረቡ በማጣራት ሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የሁመራ ትራፊክ ፖሊስ አስተባባሪ ረዳት ኢንስፔክተር ገብረጻድቃን ገብረመድህን በበኩላቸው እንዳሉት ባለ ሶስትና ባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ለትራፊክ አደጋ መባባስ ምክንያት መሆንን አስመልክቶ ከህብረተሰቡ የሚሰጠው አስተያየት ትክክል ነው።

ባለፈው ሳምንት ብቻ በሁመራ ከተማ በባጃጅና ሞተር ብስክሌት አራት የትራፊክ አደጋ አጋጥሞ ለሁለት ሰዎች ህይወት ማለፍና ለአራት ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት መድረስ ምክንያት መሆኑን በአብነት ጠቅሰዋል።

ሆኖም በአንዳንድ ሰዎች በጃጆችና ሞተር ብስክሌቶች ከስራ እንዲታገዱ የሚነሳው የንብረት እገዳ ጥያቄ ግን ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ደንብ የተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ከ900 ጊዜ በላይ ቅጣት መተላለፉን ጠቁመው አሁን ላይ በቂ የትራፊክ ፖሊሶች ባይኖሩም ህገ-ወጥ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር ሁሉንም ያሳተፈ ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

በሁመራ ከተማ ውስጥ ከ800 በላይ ባለ ሁለትና ባለ ሶስት እግር የሞተር ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙ ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም