በአገሪቷ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ቁጥር እንደማይታወቅ ተገለጸ።

127
አዲስ አበባ ጥር  13/2012 (ኢዜአ) በአገሪቷ ከሃያ ዓመት ወዲህ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ እንደማይታወቅ ተገለጸ። የዓለም የስጋ ደዌ ቀን በሀገራችን ለ21ኛ ጊዜ ጥር 16 እና 17 ቀን 2012ዓ.ም ይከበራል። በህብረተሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ በኖረ የተዛባና የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ በስጋ ደዌ ተጠቂዎች ላይ የከፋ መድልኦና መገለል ሲደርስ መቆየቱም ተገልጿል። የሰራተኛና መህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር ጋር በመሆን በዓለም የስጋ ደዌ ቀን አከባበር ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የስጋ ደዌ በሽታን ለማጥፋት በአገራችን በስፋት እየተሰራ ቢሆንም የተመዘገበው ለወጥ አናሳ መሆኑን አልሸሸጉም። በማህበሩ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ኃላፊ አቶ አሳልፈው አመዴ እንዳሉት ስጋ ደዌ በህክምና የሚድን እና በማንኛውም ሰው ላይ ሊደርስ የሚችል መሆኑ እሙን ቢሆንም የበሽታውን ሳይንሳዊ ሁኔታ ባለመረዳት ብዙ ወገኖች በወቅቱ ወደ ህክምና ተቋማት እንዳይመጡና በጊዜ ሂደት ለከፋ የአካል ጉዳት እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል። ይህ የአካል ጉዳትም በተጎጂዎች ላይ ቀድሞ የነገሰውን አድልኦና መገለል ስለሚጨምር ከሚደርስባቸው የጤና መታወክ ባልተናነሰ ለማህራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይዳርጋቸዋል፤ በመሆኑም የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ከሌላው እኩል እንዲሳተፉና እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁሉም የበኩሉን አስታዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በልዩ ትኩረት ይዞ የሚሰራበት ጊዜ በመሆኑ ማህበሩና አባላቱም መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር እና በአገር ልማት ውስጥ ድርሻቸውን ለማበርከት ጠንክረው የሚሰሩበት መሆን ይገባዋል ብለዋል። በአገሪቷ የስጋ ደዌ በሽታ ተጠቂዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ምን ያህል ተጠቂዎች እንዳሉ  በተጨባጭ መናገር እንደማይቻልና ይህን ለማወቅ ግን ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ማህበረሰቡ በጉዳዩ ላይ ያለውን ትኩረት እንዲያሳድግ በየዓመቱ ታስቦ የሚውለው ዓለም አቀፍ የስጋ ደዌ ቀን የዘንድሮው ጥር 16 እና 17 ቀን 2012ዓ.ም 'በዕውቀትና በፍቅር በተመሰረተ ሁለንተናዊ አገልግሎት በመስጠት ከስጋ ደዌ ነጻ የሆነ ማህበረሰብ እንፍጠር' በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል። በሁለቱ ቀናትም ሁለት ቀናት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በመስጠትና የፓናል ውይይት በማካሄድ እንደሚከበርም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ጌታሁን አብዲሳ ገልጸዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም