በአማራ ክልል 270ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከወደብ እየተጓጓዘ ነው

120

ባሀር ዳር ኢዜአ  ጥር 14 ቀን 2012 በአማራ ክልል ለ2012/13 የምርት ዘመን አገልግሎት የሚውል 270ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከወደብ እየተጓጓዘ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። ለክልሉ ስድስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል አፈር ማዳበሪያ ከውጭ ተገዝቶ ወደ ወደብ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የቢሮው የግብዓት ግብይትና የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ አበበ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት እየተጓጓዘ ያለው ማዳበሪያ አርሶ አደሩ በመኽር ወቅት እርሻ ጥቅም ላይ የሚያውለው ነው።

የክልሉን ግብርና ምርታማነት ለማሳደግ ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ማድረስ አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ ማዳበሪያው በአሁኑ ወቅት ወደ ክልሉ በመግባት ላይ  መሆኑን አስታውቀዋል።

ማዳበሪያው 23 ሁለገብ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች በአማካይ ቦታዎች ባዘጋጇቸው 64 መጋዘኖች በማከማቸት ለአርሶ አደሩ እንደሚያሰራጩ  ተናግረዋል።

በአዲስ የሚቀርበውንና ባለፈው ዓመት ተርፎ በየኅብረት ሥራ ማህበራቱ የከረመውን ጨምሮ በመኽር ወቅት ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውልም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።አሁን እየተጓጓዘ ያለውን ዘመናዊ ማዳበሪያ ተረክቦ በአዴትና መርዓዊ ከተሞች በሚገኙ ዘመናዊ መጋዘኖች እንደሚያከፋፍል የተናገሩት ደግሞ የመርከብ ዩኒየን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ስጦታው አባይ ናቸው።

በቀጣይም የሚረከበውን ዘመናዊ ማዳበሪያ በ135 የኅብረት ሥራ ማህበራት በኩል ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ከትራንስፖርት ድርጅቶች ተዋውለው የማዳበሪያውን መምጣት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዊ ዞን የሚገኘው የአድማስ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ መሰረት ወርቄ በበኩላቸው ከወደብ ተጓጉዞ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ ተረክበው ለመሠረታዊ አባል ማህበራት በወቅቱ ለማድረስ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ለዚህም በአንድ ዙር ብቻ 150 ሺህ ኩንታል የመያዝ አቅም ያላቸው ስምንት መጋዝኖችን እንዳዘጋጀ አመልክተዋል።

ለክልሉ ምርት ዘመን የተገዛው ማዳበሪያ ባለፈው የምርት ዘመን ከቀረበው በ800ሺህ ኩንታል ብልጫ እንዳለው ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም