ጥቃቅን፣ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አካታች የፋይናንስ ስርዓትን ለማጠናከር ቁልፍ ሚና አላቸው -- የገንዘብ ሚኒስትር

83
አዲስ አበባ ጥር  13/2012 (ኢዜአ) ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አካታች የፋይናንስ ስርዓትን ለማጠናከርና የመንግስታቱ ድርጅትን ዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካት ቁልፍ ሚና አላቸው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር  ኢዮብ ተካልኝ ተናገሩ፡፡ የተመድ አካታች የልማት ፋይናንስ ዋና ጸሀፊ ልዮ መልዕክተኛ የኔዘርላንድስ ንግስት ማክሲማ ከኢትአዮጵያ የልኡካን ቡድን ጋር በሁለተዮሽ ጉዳዮች ላይ በዳቮስ ተወያዩ። የኢትዮጵያ መንግስት የልኡካን ቡድን በሲውዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ በመሳተፍ ላይ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት አካታች የፋይናንስ ስርዓትን ለማስፋፋት ቁልፍ ሚና የሚጫወቱትን መካከለኛና አነስተኛ ተቋማት ለመደገፍና ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትር ዲኤታው በሲውዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ገልጸዋል፡፡ ‹ከግለሰብ ያለፈ አካታች ፋይናንስ፤ የጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕረይዞች ሚና› በሚል ርዕስ በፎረሙ በተካሄደው መድረክ ላይ የፋይናንስ አካታችነትን በተለይ በታዳጊ አገራት ለማስፋፋት የተያዘውን ግብ ማሳካት ይቻል ዘንድ መካከለኛና አነስተኛ ተቋማት ያለቸውን ሚና በማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ መክሯል። የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኔዘርላንዷ ንግስት ማከሲማ ሲሆኑ፣ ኃላፊነትን የተላበሰና የሰዎችን የኑሮ አቅም ያገናዘበ የፋይናንስ አገልግሎት ለሁሉም ሊደርስ እንደሚገደባ አሳስበዋል፡፡ ለአካታች የፋይናንስ መስፋፋፈት አቅጣጫ ለማስቀመጥ የተለያዩ አገራት ልምድ ለማካፈል የተካሄደው ውይይት አገራት የፋይናንስን አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማስፋፋት በሚችሉባቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ፈትሿል። የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ የትግበራ ስልቶች ላይም የሃሳብ ልውውጥ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። ዶክተር ኢዮብ በዚሁ መድረክ ላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የመካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እየተጫወቱት ያለውን ቁልፍ ሚና በማስታወቅ ዘርፉ በተልይም ለአካታች የፋይናንስ ስርዓት መስፋፋት ወሳኝ ሚና እንዳለው በመረዳት መንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን አብራርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዘርፉ ከግብርና ቀጥሎ ሁለተኛው ከፍተኛ የስራ እድል በመፍጠር ወሳኝ የምጣኔ ሃብት አውታር ለመሆን መብቃቱንም ዶክተር ኢዮብ አመላክተዋል፡፡ የመካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በተለይ ድህነትን በመቀነስና የሥራ እድልን በመፍጠር ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ካላቸው ጉልህ ሚና በመነሳትም ለአካታች ፋይናንስ መስፋፋት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለቸው ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት እኤአ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ እና የፋይናንስ አካታችነት ስልት ፈጣን የምጣኔ ሃብት እድገትን፣ ከፍ ያለ ብልጽግናንና ማህበራዊ ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ በቅርቡ አገረቱ ይፋ ባደረገችው አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ መርሃ ግብር ውስጥ ቁልፍ ምሰሶ መደረጉንም ሚኒስትር ዴታው በመድረኩ ላይ አብራርተዋል፡፡ ይህንን እውን ማድረግ ይቻል ዘንድም መንግስት ተንቀሳቃሽ የባንክ ወኪሎች አሰራር መመሪያ በማዘጋጀት፣ የብሄራዊ የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ለመፍጠር የሚያስችል ስትራቴጂ በመቀየስና አካታች የፋይናንስ ስትራቴጂውን የመከለስ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትየዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለማሻሻል የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደች በመሆኑ ወደፊት የፋይናንስ ቴክኖሎጂው አገልግሎት በከፍተኛ ፍጥነት በማስፋፋት የአገልግሎቱ ተደራሽነት ይጎለብታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ የአካታች ፋይናንስ ግቦችን ለማሳካት ተገቢ የሆኑ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብር ወሳኝነት ተሰምሮበታል፡፡ መድረኩ ከተጠናቀቀ በኋላ ሚኒስትር ዲኤታው ከተባበሩት መንግስታት አካታች የልማት ፋይናንስ ዋና ጸሀፊ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑትን ንግስት ማክሲማ ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት ኢትዮጵያ ሁሉን ተደራሽ የሆነ የፋናንስአ ቅርቦት ለመዘርጋት እያካሄደች ላለው ጥረት በፋይናንስና የተለያዩ አቅም ግንባታ የድጋፍ ፕሮግራሞችን በማሰባሰብ ለኢትዮጵያ እየሰጡ ያለውን ድጋፍና አጋርነት ዶር ኢዮብ አድንቀው ምስጋናቸውን ለንግስቲቱና ከእርሻቸውጋር ለሚሰሩ አጋሮች አቅርበዋል፡፡ በዘንድሮው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ከ3,000 በላይ የሚገመቱ ከተለያዮ የዓለም ክፍሎች በመጡ የታላላቅ መሪዎች፤ የባንክ ገዚዎች፤ የፋይናስ ባለሙያዎች እና ኢንቪስተሮች እየተሳተፉ መሆኑ ታውቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም