የአፋርና የአማራ ክልሎች የሰላም ኮንፍረንስ ተጀመረ

56
ሰመራ ጥር 13 / 2012 (ኢዜአ) የአፋርና የአማራ ክልል አጎራባች ወረዳዎች የሰላም ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው። በአፋር ክልል አደአር ወረዳ እየተከናወነ ባለው ኮንፍረንስ ከክልሎቹ 14 ቀበሌዎች የተውጣጡ 2ሺህ የሚጠጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተካፍለዋል። በኮንፈረንሱ ከአማራ ክልል ባቲ፣ ከአፋር ክልል የአደአር፣ ተላላክ፣ ደዊና ጭፍራ ወረዳዎች የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች ፣ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም አመራሮች ተሳትፈዋል። በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሰን እንደተናገሩት ሁለቱ ወንድማማችና ህዝቦች ከሚለያቸው ነገር በላይ የሚያገናኟቸው የጋራ እሴቶች አሏቸው። ሕዝቦቹ ለጋራ ልማትና ሰላም በመታገል ሕይወታቸውን ለመለወጥ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። የአፋር ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቢላይ አህመድ በበኩላቸው የአፋር ህዝብ ከአጎራባች የአሮሞ ማህብረሰብ ጋር በጋብቻ ጭምር የተሳሰረ ወንድማማች ሕዝብ መሆኑን አመልክተው፣አብሮነቱን የማይፈልጉ አካሎች የተለያዩ ሴራዎችን በመሸረብ ሲያጋጯቸው መቆየታቸውን ገልጸዋል። በሕዝቦች መካከል ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር ከአመራር እስከ ኅብረተሰቡ ያሉት አካላትን ያሳተፈ ኮንፍረንስ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። ሕዝቦቹ ለዘመናት የገነቡትን አብሮነት ለማስቀጠል ከመንግሥት ጋር በቅርበት መሥራትና ችግር የሚፈጥሩባቸውን አካላት ለሕግ እንዲያቀርቡ አስገንዝበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም