የደራሼ ልዩ ወረዳ የባህልና የ''ፊላ'' ፌስቲቫል በጊዶሌ ተጀመረ

58
ዓርባ ምንጭ  ጥር 13/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የደራሼ ልዩ ወረዳ ሁለተኛው የባህልና የ''ፊላ'' ፌስቲቫል በጊዶሌ ከተማ ዛሬ ተጀመረ፡፡ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ፌስቲቫል''ፊላ'' የተሰኘው የደራሼ ብሔረሰብ ባህላዊ የትንፋሽ መሣሪያ ጨዋታን ጨምሮ የኩስሜ፣ የማሾሌና የሞስዬ ብሔረሰቦች ባህላዊ ሙዚቃዎችይቀርባሉ። ባህላዊ ምግቦች፣ አልባሳትና የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ የፌስቲቫሉ አካል መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በፌስቲቫሉ በፊላ ሙዚቃ መሣሪያና በማሾሌ ሕዝቦች ታሪክ ላይ የሚያተኩሩ ሁለት መጻህፍት ይመረቃሉ፡፡ የልዩ ወረዳው ባህላዊ የእህል ጎተራና የመሬት ለምነት አጠባበቅ ዘዴዎች ጨምሮ  ታሪካዊና ባህላዊ ስፍራዎች ይጎበኛሉ፡፡ የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲርቦ ሲሳይ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች የሕዝቡ የጋራ ሀብት በመሆናቸው በአብሮነት መልማት አለባቸው ብለዋል። ቅርሶቹ ከኢኮቱሪዝም ልማት ባለፈ የሕዝቡን አንድነት ለማጠናከር ያላቸውን ፋይዳ ለማስተዋወቅ ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በዝግጅቱ የደቡብ ክልል መንግሥት ባለስልጣናት፣ ምሁራን፣ የአካባቢው ተወላጆች ተገኝተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም