የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከ192 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

135

አዲስ አበባ ጥር 13 ቀን 2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ከትራፊክ ፍሰትና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከ192 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ። በአዲስ-አዳማ እና በድሬዳዋ ደወሌ የፍጥነት መንገዶች ከአራት ሚሊዮን በላይ የትራፊክ ፍሰት ተስተናግዷል።

በዚህም ኢንተርፕራይዙ ከ181 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሰበሰበ ሲሆን የማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ለኢዜአ በላከው መረጃ ያረጋገጠው።

ኢንተርፕራይዙ በአዲስ-አዳማና ድሬዳዋ-ደወሌ የክፍያ መንገዶች ያልተቋረጠ የ24 ሰዓትና የ7 ቀናት የክፍያ መንገድ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ይሁንና በድሬደዋ-ደወሌ መንገድ ላይ ያለው የክብደት ቁጥጥር አስተማማኝ ባለመሆኑ ከክብደት በላይ ጭነው የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች እያደረሱ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በቀጣይ በኢንተርፕራይዙ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተገልጿል።

ኢንተርፕራይዙ የክፍያ መንገድ ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀትና በመንገዱ ክልል ውስጥ የ24 ሰዓት የመንገድ ቅኝታዊ ቁጥጥር ማድረጉን አስታውቋል።

በዚህም በትራፊክ አደጋ የሚደርስ ሞትን 50 በመቶ መቀነስ የተቻለ ሲሆን አምና በተመሳሳይ ወቅት በአዲስ-አዳማ የክፍያ መንገድ በትራፊክ አደጋ 12 የነበረው የሞት አደጋ በግማሽ መቀነስ ተችሏል።

በክፍያ መንገዶች ላይ ከተፈቀደው ክብደት በላይ የሚጭኑ አሽከርካሪዎች የሚቀጡበት ህግ ባለመኖሩ የመንገዱን ደህንነት ለማስጠበቅ ኢንተርፕራይዙ መቸገሩን ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም