በደብረ ብርሃን መስኖ ግድብ ውስጥ ለመዋኘት የገቡ ህፃናት ሕይወት አለፈ

98

ደብረ ብርሃን ጥር 13 ቀን 2012 (ኢዜአ) በደብረ ብርሃን ከተማ መስኖ ግድብ ውስጥ ለመዋኘት የገቡ ሦስት ህፃናት ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

በከተማው የአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ምንውየለት ጭንቅሎ ለኢዜአ እንዳስታወቁት የሕፃናቱ ሕይወት ያለፈው አሳስ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኝ ግድብ ውሰጥ ለመዋኘት ሲሞክሩ ነው።

ሕፃናቱ ለሞተ የተዳረጉት ከጥምቀት መልስ በግድቡ ለመዋኘት በገቡበት ወቅት መሆኑንም አመልክተዋል።

የጓደኞቹን መስመጥ የተመለከተው ጓደኛቸው ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ መሠረት የሁለቱ ሕፃናት አስከሬን ትናንት አመሻሽ ላይ ተገኝቷል።

የአንደኛው ህፃን አስክሬን ፍለጋ  መቀጠሉንም ኢንስፔክተር ምንውየለት ገልጸዋል።

ሟቾቹ የሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች እንደነበሩም ተመልክቷል።

የሟቾቹ አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው እንዲደርስ ተደርጎ ዛሬ ሥርዓተ ቀብራቸው እንደሚፈጸም ኃላፊው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም