ክልሉ ሰላምን ለማረጋገጥና ለተፈጥሮ ሀብት ልማት ትኩረት እንዲሰጥ የምክር ቤት አባላት አሳሰቡ

60
አሶሳ ጥር 13/2012  (ኢዜአ)  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥና ለተፈጥሮ ሀብት ልማት ትኩረት እንዲሰጥ የክልሉ ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ። ምክር ቤቱ አምስተኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባዔ ትናንት ምሽት ተጠናቋል። ጉባዔው ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት አጽድቋል። የምክር ቤቱ አባላት በጉባዔው ሰላምን በዘለቄታው በማረጋገጥና ለተፈጥሮ ሀብት ልማት ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዝበዋል። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ አልከድር አህመድ እንዳሉት አስፈፃሚው አካል የአገሪቱን ሰላም በማናጋት የህዝቦችን አንድነት ለመናድ የሚጥሩትን ለማስቆም በትጋት መስራት አለበት ። ሙስናና በመዋጋትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መሰራት እንደሚገባው አመልክተው፣እየጨመረ የመጣውን የተማረ የሰው ኃይል በመጠቀም የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ማልማት እንደሚገባ ተናግረዋል። በዚህም ሕዝቡን ከድህነት ማላቀቅ እንደሚቻል እምነታቸውን ገልጸዋል ። በመተከል ዞን ግንባታው ሳይጠናቀቅ ለረጅም ዓመታት የቆየ መንገድ መኖሩን የተናገሩት ደግሞ አቶ ግርማ መኒ የተባሉ የምክር ቤት አባል ናቸው። በክልሉ በትራንስፖርት እጦት ምርታቸውን ለገበያ የማያቀርቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚገኙ አመልክተዋል። ለኢንቨስመንት የሚውል መሬት በማሰተላለፍ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል። ግጭት በተከሰተባቸው አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የተደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች ውጤት ቢያመጡም፣ ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ ረገድ ያለው ችግር የፈጠረውን ስጋት መፍታት ያስፈልጋል ሲሉ አሰተያየታቸውን ሰጥተዋል። አቶ ጌታነህ ሰዲ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ደግሞ እየተስፋፋ የመጣው ህገወጥ የመሬት ወረራ ለማስቆም ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ''በኢትዮጵያዊነታችን አንደራደርም'' ያሉት አቶ ታመነ በሌ  በበኩላቸው በአየር ትራንስፖርት ካልሆነ በቀር አጎራባች ክልሎችን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ  አሁንም አስቸጋሪ መሆኑ መፍትሄ እንዲፈለግለት ጠይቀዋል። በአሶሳና ካማሽ ዞኖች  የነበረው የፀጥታ ችግር መሻሻል ቢያሳይም፤ በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ በታጠቁ ኃይሎች የሚፈፀመው ዘረፋና ግድያ አልቆመም ያሉት አቶ ሽፈራው ጨሊቦ ናቸው። የችግሩ ምንጭ የፀጥታ ኃይሎችን በቅንጅት ለመምራት ባለመቻሉ እንደሆነም ጠቅሰዋል። የዋጋ ንረት፣ በሙስናና በክትትል እጦት የሚፈጠር የመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ መጓተት ፣ ህገወጥ የወርቅ ምርትና ዝውውርን መግታት የክልሉ መንግስት ሊያስተካክላቸው የሚገባቸው ሌሎች ጉዳዮች እንደሆኑ በምክር ቤት አባላት ተነስተዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ለችግሮቹ የበጀት እጥረት፣ የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ፣ የባለሙያዎች ድክመትና ኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል። የግንባታ ጥራት ማነስና አቅምን አሟጦ አለመጠቀም ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸውን አመልክተዋል። የክትትል ማነስ ችግር የታየባቸው ተቋማት እንዲያስተካክሉ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ሥራ መገባቱን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት በተለይ በባህላዊ መንገድ የሚመረተው የወርቅ ሀብት መዳረሻ ለማወቅ እየሰራ መሆኑን  ተናግረዋል። በቀጣይ ወራት በጉባዔው ለተነሱት ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ትኩረት ይሰጣል ብለዋል። ለውጤታማነቱ የሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የህዝቡ ድጋፍ እንዳይለያቸው  አቶ አሻድሊ ጠይቀዋል። የምክር ቤቱ አባላት ለክልሉ ተጨማሪ በጀት የተጠየቀውን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ አፅድቀዋል። እንዲሁም በምክር ቤቱ የአሰራርና የስነ ስነምግባር ደንብ መሠረት በግጭት ተጠርጥረው በህግ ጥላ ሥር ከቆዩ በኃላ ጉዳያቸው ተጣርቶ በነፃ የተሰናበቱት የምክር ቤት አባል አቶ ባበክር ከሊፋን ያለመከሰስ መብት እንዲመለስ በሙሉ ድምፅ ወስነዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም