የጥምቀት በዓል ላይ ሁከት ለመፍጠር የሞከሩ አካላት ለህግ ይቀርባሉ…አቶ ኦርዲን በድሪ

518

ሀረር፤ ጥር 13/2012 (ኢዜአ) ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ በሀረር ከተማ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ለደረሰው ጉዳት መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስድ የሀረሪ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

ርዕሰ-መስተዳድሩ በክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ለበዓሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አስፈላጊው ዝግጅት ቢደረግም ግጭት የመፍጠር ተልዕኮን ባነገቡ አካላት በተፈጸመ ተግባር በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ሃዘን የገለጹት ርዕሰ-መስተዳደሩ፣ መንግስት ለተጎጂዎች ተገቢውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም አሳውቀዋል።

በቀጣይም በድርጊቱ የተሳተፉ፣ በተለያየ መንገድ ሲመሩና ሲደግፉ የነበሩ አካላትን የክልሉ የፀጥታና ፍትህ አካላት በአፋጣኝ አጣርተው ለፍርድ በማቅረብ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ በትኩረት እንደሚከናወን ገልፀዋል።

ሕብረተሰቡ ላሳየው ትዕግስትና ከጸጥታ አካላት ላደረገው ትብብር በራሳቸውና በክልሉ መንግስት ስም ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ኦርዲን በድሪ በቀጣይም ከመንግስት ጎን በመቆም አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የክልሉ የጸጥታ አካላት የበዓል አከባበሩን በማወክ የተጠረጠሩ ከ20 የሚበልጡ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን በትናንትና መዘገባችን ይታወሳል።