ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር አለመውደቋ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ስርዓቷ ሳይበረዝ እንዲቆይ አስችሏል – የውጭ አገራት ጎብኝዎች

238

አዲስ አበባ ጥር 12/2012 ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር አለመውደቋ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ስርዓቷ ሳይበረዝ እንዲቆይ ማስቻሉን ባሕረ ጥምቀት የታደሙ የውጭ አገራት ጎብኚዎች ተናገሩ።

በዓለም የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት መዝገብ የሰፈረው የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ላይ በርካታ የውጭ አገራት ጎብኚዎች ተሳትፈዋል።

በአደባባይ ከሚከወኑ በዓላት መካከል አንዱ በሆነው የጥምቀት ክብረ በዓል መታደማቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል ጎብኚዎቹ።

የበዓሉ አከባበር የኢትዮጵያን የረጂም ጊዜ ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ መከበሩ፣ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻቸው ለትውልድ ማስተላለፍ በመቻላቸው የተሻገረ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የስዊዲን አምባሳደር ቶርብዮርን ፔተርሰንን ጨምሮ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት ኢትዮጵያ የከተሙ እንግዶች ኢትዮጵያ እንደ ጥምቀት አይነት ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ጎልተው የሚወጡበት ክብረ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

በክብረ በዓላት የሚከወኑ ትውፊታዊ ስርዓቶች ለዘመናት ሳይበረዙ የመቆየታቸው ምስጢር አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሳትወድቅ በሉዓላዊነት ለዘመናት መኖሯ እንደሆነም ይናገራሉ።