የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ኢትዮጵያ ያሏት እምቅ ታሪካዊ ሀብቶች ዓለም እንዲያውቅ የሚያደርግ ነው- ቱሪስቶች

64
አዲስ አበባ ጥር 12/2012 (ኢዜአ)  የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ ታሪካዊ ሀብቶች ዓለም ይበልጥ እንዲያውቅ የሚያደርግ እንደሆነ ቱሪስቶች ገለጹ። የጥምቀት በዓል በመላ አገሪቷ በተለይም በጃን ሜዳ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ዛሬ በድምቀት ተከብሯል። ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዞ በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበትን ዕለት በማሰብ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ ከዋዜማው የከተራ በዓል ጀምሮ ጥር 11 የእምነቱ ተከታዮች በደማቅ ሁኔታ በተለያዩ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ስነ-ስርአቶች ያከብሩታል። የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ የተከበረ ነው። ኢዜአ ያነጋገራቸውና በዓሉ ላይ የታደሙ ቱሪስቶች የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ጥምቀትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች ይበልጥ ዓለም እንዲያውቀው ከማድርግ አኳያ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ቶርብዮርን ፔተርሰን በጥምቀት በዓል ላይ ሲታደሙ ለሶስተኛ ጊዜ እንደሆነና በዓሉ ኢትዮጵያ ያላትን ለዘመናት የቆየውን ሃይማኖታዊ ትውፊት የሚያሳይ ነውም ብለዋል። ዩኔስኮ ልዩ የሆነ ባህላዊ ገጽታ ያለውን የጥምቀት በዓልን በቅርስነት መመዝገቡ ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ ታሪካዊ ሀብቶች ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራልም ብለዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ አገራት ብዙ ታሪካዊ ሀብቶች ያሏት መሆኗና የጥምቀት በዓሉም ዓለም አቀፋዊ እውቅና ማግኘቱ ለበዓሉ የሚመጡ ቱሪስቶችን ቁጥር እንደሚጨምረውም አመልክተዋል። በስዊድን በሚገኘው የኦርቶክስ ቤተክርስቲያን የጥምቀት በዓል እንደሚከበር የገለጹት አምባሳደሩ፤ በኃይማኖት አባቶች የተባረከውን ውሃ ለእምነቱ ተከታዮች መርጨት በአገራቸው ክብረ በዓል ላይ እንደሌለና ይሄም ለበዓሉ ልዩ ገጽታ የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል። አሜሪካዊው ፖል ሜየር በጥምቀት በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ መታደማቸውንና በዓሉ ብዙ ህዝብ በአንድ ጊዜ አንድ ቦታ ላይ ተሰብስቦ የሚያከብረው መሆኑ በዓሉን ለየት እንደሚያደርገው ተናግረዋል። የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገብ ኢትዮጵያ ሯሷን ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ እድል ይሰጣታልም ብለዋል። በጥምቀት በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ የታደሙትና ከስኮትላንድ የመጡት ሚስ አን ሜይ በበኩላቸው "በበዓሉ ላይ የታደሙት ሰዎች ያላቸው ደስታና አብሮነት በጣም አስደንቆኛል" ብለዋል። ኢትዮጵያ ያላትን የአብሮነት ባህልና መንፈሳዊ ስርዓቶቿንም ዓለም ማየት እንደሚገባውና ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ወቅትም ይሄንኑ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ገልጸዋል። ደቡብ ኮሪያዊው ዳዊት ሶንግ በኢትዮጵያ መኖር ከጀመረ ዘጠኝ ዓመት አንደሆነውና ስምንቱንም ዓመት በጃን ሜዳ የጥምቀት በዓል ላይ እንደታደመ ይገልጻል። ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገቡ የውጭ አገር ዜጎች በበዓሉ የመታደም ፍላጎታቸውን እንደሚጨምረውና በተለይም በአገሩ ያሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉን ለመታደም ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል ብሏል። ኢትዮጵያ በኃይማኖትና በባህል ያላትን ታሪኮች ለተቀረው ዓለም እንደ ተሞክሮ ማካፈል ብትችልም መልካም ነው ብለዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም