ለአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነትና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለመሆን የሚወዳደሩ እጩዎች ይፋ ሆኑ

61
አዲስ አበባ ጥር 12/2012 (ኢዜአ) ለአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነትና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለመሆን የሚወዳደሩ እጩዎች ይፋ ሆነዋል። ለስራ አስፈጻሚነት እጩ ለመሆን አመልክተው ከነበሩ እጩዎች መካከል ሁለቱ በተለያዩ ምክንያቶች ዝርዝር ውስጥ ሳይካተቱ ቀርተዋል። እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጥር 16 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን የሚያካሄድ ሲሆን ከጉባኤው አጀንዳዎች መካከል ፌዴሬሽኑን የሚመራ ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መምረጥ ነው። በዚሁ መሰረት ፌዴሬሽኑ በፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ አራት በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትነት የሚወዳደሩ ደግሞ 17 እጩዎችን ይፋ አድርጓል። በዚሁ መሰረት የወቅቱ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሃይለየሱስ አለማየሁ፣ ዶክተር ጊዮን ሰይፋ፣አቶ ዳንኤል ሽፈራውና አቶ ዮሐንስ መዝገቡ በፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ እጩዎች ናቸው። ዶክተር አይናለም አባይነህ፣ ዋና ኢኒስፔክተር የኔነህ በቀለ፣ ወይዘሮ ሰርካለም ከበደ፣ አቶ ብርሃኑ ከበደ፣ አቶ አፈወርቅ አየለ፣ አቶ ሃይሉ ወልዴ፣ አቶ ወንደሰን ተሰማ፣ ወይዘሮ ህይወት አራጌ፣ አቶ ሳልለው አበራ፣ አቶ ሰመረአብ ሳህሌ፣ አቶ ዳኛቸው በላይ፣ አቶ ብርሃኑ ደምሴ፣ አቶ ደረጄ ወርቁ፣ አቶ ይርጋለም ንጉሴ፣ አቶ ደመላሽ ደስአለኝ፣ አቶ ድሪባ ኪታባና አቶ ደጀኔ ሃይለመስቀል ደግሞ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የሚወዳደሩ እጩዎች ናቸው። በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ለመወዳዳር አመልክተው የነበሩት የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በለጠ ዘውዴና አቶ መኮንን አስረስ በተለያዩ ምክንያቶች በእጩዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ሳይካተቱ ቀርተዋል። የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፈለቀ ዋቄ አቶ በለጠ ዘውዴ በእጩዎች ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱት "የፌዴሬሽኑ አሰራር አልተመቸኝም" በሚል ከውድድሩ እራሳቸውን ማግለላቸውን ለፌዴሬሽኑ የጻፉትን ደብዳቤ ተከትሎ ነው ብለዋል። የእጩዎች አጣሪ ኮሚቴ አቶ በለጠ ዘውዴ ሁለት ቦታ እየሰሩ በመሆናቸው የስፖርት ማህበራት መመሪያው ይሄን የማይፈቅድ በመሆኑ ከእጩነት ዝርዝር አስወጥቷቸው እንደነበረና በኮሚቴ ላይ የአሰራር ክፍተት እንደታየ ገልጸዋል። የአሰራር ክፍተቱ እጩው አንደኛውን ስራቸውን በመተው በእጩነት መወዳዳር እንደሚችሉ እንደሚያስቀምጥ የኮሚቴው ውሳኔ ከዚህ አንጻር ስህተት እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ በለጠ ዘውዴ በጻፉት ደብዳቤ ላይ "እኔ አንዱን ስራ ትቼ መወዳደር እችላለሁ ነገር ግን የፌዴሬሽኑ አሰራር ስላልተመቸኝ ነው በምርጫው ላይ የማልወዳደረው" ማለታቸውን አመልክተዋል። አቶ መኮንን አስረስም ሁለት ቦታ እየሰሩ በመሆናቸውና አንዱን ስራ ባለመተዋቸው ከእጩዎች ዝርዝር ውስጥ አለመካተታቸውን ነው አቶ ፈለቀ ያስረዱት። ለምርጫው የተቋቋሙት ኮሚቴዎች የወጣው ዝርዝር እንዳለ አሁንም በእጩዎቹ ተገቢነት ላይ ማጣራት እንደሚያደርግና በጠቅላላ ጉባኤው ወቅት እንደሚያሳውቅ አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም