ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙባቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተሳትፎን ይጠይቃል ... ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተንኩዋይ

52

ጋምቤላ ጥር 12 ቀን 2012 ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙባቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተሳትፎ መጠናከር እንደሚገባው የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ፡፡

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲና የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር የጥምቀት በዓልን በማስመልከት ለተማሪዎች የምሳ ግብዣ አድርገዋል።የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችም በዓሉን በጋራ አክብረዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ተንኩዋይ ጆክ በዚሁ ወቅት እንዳስገነዘቡት ተቋማቱ ዓላማቸው እንዲያሳኩና ስኬታማ እንዲሆኑ የማህብረሰቡ ሚና መጎልበት አለበት፡፡

በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ከዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ ባሻገር የአካባቢው ኅብረተሰብ ሚና ቀላል እንዳልሆነ  አመልክተዋል፡፡

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ውጤታማ የሚሆነው የአካባቢው ነዋሪዎች በሚያደርገው አስተዋጽኦ ታግዞ መሆኑንም አቶ ተንኩዋይ ገልጸዋል፡፡

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ እንዳሉት ግብዣው ተማሪዎቹ በዓላትን ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከአመራሩ ጋር አብሮ እንዲያሳልፉ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

መሰል ዝግጅቶች በተማሪዎችና በአካባቢው ማህብረሰብ ዘንድ ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ቀጣይነት  ያረጋግጣሉ ብለዋል፡፡

የአንድነትና የአብሮነት ትስስሮኙ እንዲጠናከር ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ጽዮን ጳውሎስ እንዳለችው በዓሉን ከክልሉ አመራሮችና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ማክበሯ እንዳስደሰታት ገልጻለች።

ዝግጅቱ በተለይም በበዓላት ወቅት የሚያጋጥውውን የቤተሰብ ናፍቆት የሚያስረሳ ነበር ብላለች፡፡

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ላለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ዋነኛ ተዋናዩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አንድነትና አብሮነት ቢሆንም፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ሚና ዋጋ እንዳለው የገለጸው ደግሞ ተማሪ ገልገሎ ሚኪያስ ነው፡፡

በተለይም የአካባቢው ነዋሪዎችና አመራሮች በዓላትን ከተማሪዎች ጋር ማሳለፋቸው አብሮነትን በተግባር እንዳሳየ ተናግሯል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የሐይማኖት አባቶች፣የአገር ሽማግሌዎችና እንግዶች ታድመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም