የጥምቀተ ባህሩ ገጽታዎች

49
አዲስ አበባ ጥር 11 / 2012(ኢዜአ )ጥምቀት ዘንድሮ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፤ ልዩ ገጽታም ተላብሷል። የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ይዘቱን ስንመለከት፤ የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውሰው እለት ነው። ትርጉሙም መገለጥ፣ መታየት ማለት ነው በማለት መፅሓፍ ቅዱስ ላይ ተቀምጧል። የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀተ ታሪክን ለመዘከር በኢትዮጵያ የሚገኙ ክርስቲያኖችም በተለያዩ መልኩ ያከብሩታል። በየዓመቱ ጥር 10 እና 11 በደማቅ ሁኔታ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ይከበራል። በዓሉ ከከተራ ወይም ከዋዜማው ጀምሮ ደማቅ ገዕታን ይላበሳል። በከተራ ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባህሩ ይወርዳሉ። በገጠር ይሁን በከተማ ወራጅ ውኃ ያለበትና ያቆረ ውኃ ባለበት አካባቢ ታቦታቱ ከአብያተ ክርስትያናቱ ተነስተው በምዕመናኑ ታጅበው ጉዞ ያደርጋሉ። ጉዞው በዝማሬ፣ በውዳሴ፣ በሆታና በጭፈራ የታገዘ በመሆኑም የእምነቱ ተከታዮች ነጫጭ የአገር ባህል ልብስ ለብሰው ታቦታቱን ያጅባሉ። ትናንትም በመላ አገሪቷ የሆነው ይህ ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በርከት ብለው በሚኖሩበት ሁሉ ሓሴት ነበር። ጎንደርን እንመልከት፤ ትልቁና የጥምቀት ባዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው የአገሪቷ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው። በጎንደር የጥምቀት ባዓልን ለመታደም ርዕሰ ብሔሯ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ በርካታ የአገር ውስጥና የአገር ውጭ ታዳሚያን በከተራ ላይ ታዳሚ ነበሩ። ሌላው የጎንደርን ከተራና ጥምቀትን ለየት የሚያደርገው ሰላም ወዳዶቹ የጋሞ አገር ሽማግሌዎች ''ከጋሞ እስከ ጎንደር የሰላም ጉዞ'' ብለው የበዓሉ ታዳሚ መሆናቸው ነበር። በጥቅሉ ጎንደር ከከተራ እስከ ጥምቀት ጎንደርን የሚገልጹ ገጽታዎችን ተላብሳ በተለያዩ ክንውኖች አሸብርቃና ደምቃ የጥምቀት በዓለን እያከበረች ትገኛለች። ጥምቀት ሲነሳ የአዲስ አበባው ጃን ሜዳ በዓይነ ህሊና ትልቅ ስፍራ ይይዛል። ጃን ሜዳ ለ100 ዓመታት ገደማ ጥምቀትን አድምቋል። በርካታ ሕዝብ በታደመበት የጃን ሜዳው የባዓል አከባበር ላይ ሀርሞኒካን ጨምሮ በርከት ያሉ ባህላዊ ጨዋታዎች ደምቀውበታል። ወጣቶችም ቆንጀተው ታይተውበታል። ጃን ሜዳ ከልብ በመነጨ አብሮነትና ፍቅር የታጀበ ህብር የሚታይበትም ነው። በዚሁ ስፍራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማትያስ የፍቅርን ኃያልነት ሰብከውበታል፤ ምዕመኑም በዚሁ መርህ እንዲኖሩ አሳስበዋል። የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማም በመዲናዋ ስም በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን ጥምቀት ለመጠበቅና ለመንከባከብ እንደሚተጉ ለምዕመኑ ቃል ገብተዋል። በዓሉ ላይ የተላያዩ አገራት ጎብኚዎች እየታደሙ ይገኛሉ። ጎብኚዎቹ ተደንቀወዋል፤ ተደምመዋል፤ ኢትዮጵያውያንንም አሞካሽተውበታል። ይህ የተለመደ ቢሆንም አገሪቷ ያልተበረዘ የበዓላት አከባበርን ይዛ መቀጠሏ አስደንቀቸዋል። ዘንድሮ የሰላም ሁኔታውም የተሻለ ሊባል ይችላል። በተወሰኑ የአገሪቷ አካባቢዎች 'ባንዲራን' መነሻ ያደረጉ ውጥረቶች ከመንገሳቸው ውጪ ጥምቀት እንደ ደመቀና እንዳሸበረቀ ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም