ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር ለአገራቸው ብልጽግና መረጋገጥ ተግተው ሊሰሩ ይገባል... የውጭ ዜጎች

70
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 10/2012 ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር ለአገራቸው ብልጽግና መረጋገጥ ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባ በጥምቀት ከተራ በዓል ላይ የተገኙ የውጭ ዜጎች ተናገሩ። ኢትዮጵያዊያን በይበልጥ አንድ ሆነው ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ታሪካዊ አገራቸውን ለማቆየት መስራት እንደሚኖርባቸውም አስተያየት ሰጥተዋል። ከጣሊያን የመጡት ሚስተር ጆውን ፒተርሰን ለአራተኛ ጊዜ በዚህ በዓል ላይ ለመታደም መቻላቸውን ተናግረው፤ ''አገሪቱ አሁን በጥሩ መስመር ላይ የምትገኝ በመሆኑ ብልጽግናዋን ለማምጣት ተግቶ መስራት ይገባል'' ብለዋል። በአሜሪካ የጥምቀት በዓል በእንደዚህ መልኩ እንደማይከበር የገለፁት ሚስተር ስቲቭ ማርክ ደግሞ የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ የተለየ ድምቀት እንዳለው ገልፀዋል። ወደ ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት በፊት መምጣታቸውን የተናገሩት ሚስተር ስቲቭ በቆይታቸው መልካም ነገሮችን ለመታዘብ መቻላቸውን ተናግረዋል። ከታዘቧቸው ነገሮች መካከል በዛሬው እለት በተከበረው የጥምቀት ከተራ በዓል የተለያዩ አለባበስ ያላቸው ህዝቦች በአንድነት ሲያከብሩ ልዩ ድምቀት እንደፈጠረ ገልፀዋል። ከአሜሪካ የመጡት ሚስተር ዋልተር ዋከር እና ባለቤታቸው ሚስ ሱዛን ዋከር በበኩላቸው ይሄን በዓል ለማክበር እዚህ መገኘታቸውን ተናግረዋል። ''አንድነት ጠቃሚ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን አንድ በመሆን ጠንካራ አገር እንዳላቸው ማሳየት ይገባቸዋል'' ብለዋል። ከአሜሪካ ቴክሳስ የመጣችው ጃክሊን ማክስ በበኩሏ እዚህ ከመጣች አንድ ወር  እንደሆናት በመግለጽ በቆይታዋ ኢትዮጵያዊያን ላይ ትልቅ አንድነት መመልከቷን ገልጻለች። በቆይታዋ በርካታ ወዳጆችን ማፍራት መቻሏን እና ያለውን ፍቅርና አንድነት ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግራለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም