የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር የኢትዮጵያዊያንን የአብሮነት እሴት የሚያሳይ ነው… የበዓሉ ታዳሚዎች

201

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2012 (ኢዜአ)የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ኢትዮጵያዊያን የሚጋሩትን ጠንካራ የአብሮነት እሴት የሚያሳይ መሆኑን የከተራ በዓልን በአዲስ አበባ እያከበሩ ያሉ  ተሳታፊዎች ገለጹ።

የከተራ በዓል ዛሬ በመላ ኢትዮጵያ በድምቀት ተከብሯል።

በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በተከበረው የከተራ በዓል ላይ ሲሳተፉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች በዓለ ጥምቀት ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን የህዝቦች አንድነት መገለጫ ደማቅ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

የጥምቀት በዓል በተለይም በኢትዮጵያ ኦቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል።

ዛሬ የተከበረው የከተራ በዓል ታቦታት ከየአብያተ-ክርስቲያናቱ ወጥተው ወደየማደሪያቸው ባህረ-ጥምቀት ሲሸኙ በዝማሬና በሽብሸባ ይታጀባሉ።

የበዓሉ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊነቱ ባሻገር ኢትዮጵያዊያን የሚጋሩትን ጠንካራ የአብሮነት እሴት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የቀጨኔመድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን አገልጋይ መምህር ሸዋአገኘው ከበደ በበዓሉ የሚታደሙት የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች እምነት ተከታዮች ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

”ይህም ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበት የብሮነት መስተጋብር የሚያንጸባረቅበትና መቀጠል ያለበት ነው” ብለዋል።

አቶ ታሪኩ ገብረህይወት በበኩላቸው ከጥንት ጀምሮ በአብሮነት የተጓዝንበት መንገድ ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም ወገን በመከባበርና በመቻቻል መኖር እንደሚገባው ተናግረዋል።

ሌላዋ የበዓሉ ታዳሚ ወይዘሮ አገሪቷ አበበ በሰጡት አስተያየት ወጣቱ ትውልድ ከዘመናት በፊት የነበረውን የአብሮነት እሴት አስጠብቆ ለማስቀጠል መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።

አቶ ድልነሳው መላኩ ባነሱት ሃሳብ ”የጥምቀት በዓልን ጨምሮ ሌሎች በርካታ በዓላትን ስናከብር ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር በመሆን ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ትውልዱ የአብሮነት ማስተሳሰሪያ እሴቱን የሚያሳጣውን ተግባር በመተው መልካሙን በማጽናት መጓዝ እንደሚገባው አመልክተዋል።

ዛሬ የተከበረው የጥምቀት የከተራ በዓል በርከታ የእምነቱ ተከታዮች እና ከውጭ አገሮች የመጡ ቱሪስቶች ጨምሮ ሌሎችም ታድመውበታል።