በአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞች የከተራ በዓል ተከብሯል

125

ባህር ዳር ጥር 10/ 2012 (ኢዜአ)  በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የከተራ በዓል በአማራ ክልል  ከተሞች ተከብሯል።

በዓሉ በባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃንና ሌሎች ከተሞች ተከብሯል።

በባህር ዳር ከተማ በዓሉን የተደራጁና መለዮ የለበሱ ወጣቶች ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመተባበር በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር ሚናቸውን ተወጥተዋል።

በተለይም ታቦታቱ የሚጓዙባቸውን ጎዳናዎች በማፅዳት፣ በውሃ በማጠብና የማረፊያ ቦታዎችን ንጽህና በመጠበቅ ድርሻቸውን ተወጥተዋል።

በባህርዳር ከተማ በተከበው የከተራ በዓል ላይ የባህር ዳር ከተማ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን ከክፋት ይልቅ ደግነትን ትናንት፣ ዛሬና ነገም ቢሆን ታስተምራለች ብለዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ዶክተር መሃሪ ታደሰ በበኩላቸው ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በሰላምና ልማት ዙሪያ በጋራ ተጋግዘን እንሰራለን ብለዋል።

ኅብረተሰቡ የከተራ በዓልን በትብብር ለማክበር እንደሰራው ሁሉ፤ በሌሎች የአንድነት፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ጉዳዮች በጋራ መስራትእንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በበዓሉ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅ ሰሙ ማሞና ሌሎች ከፍተኛ በለሥልጣናት ተገኝተዋል።

በጎንደር በተካሄደው በዓል ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኤርትራ ልዑቡድን፣ የጋሞ አባቶችና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የጥምቀት በዓል ነገ በተለይ በጎንደር ከተማ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የውጭና አገር ውስጥ ተሳታፊዎች በሚገኙበት ይከበራል።