የህዳሴ ግድብ ድርድር ልዑክ ቡድን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጻ አደረገ

1294

አዲስ አበባ ጥር 10/2012 (ኢዜአ)  በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በዋሽግተን ዲሲ ድርድር ያካሄደው የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን የድርድር ሂደቱን በአጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጻ አደረገ።

የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች እና የልዑካን ቡድኖቻቸው በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ድርድር ማድረጋቸው ይታወሳል።

በመድረኩም የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቬን ሙንሺን እና የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ  በታዛቢነት ተሳትፈውበታል።

አገሮቹ እስካሁን በተደረጉ ድርድሮች በልዩነት የሚያነሷቸውን ሃሳቦች በሚመለከትም በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ መፍታት በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ ተወያይተው መግባባት ላይ መድረሳቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

በድርድሩ የተሳተፈው የልዑክ ቡድን በድርድሩ የተገኙ ድሎችና የቀጣይ አካሄዶችን በሚመለከት ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ አድርጓል።

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በገለጻው ወቅት እንዳሉት፤ በድርድሩ አገሮቹ በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን ልዩነት ማጥበብ ተችሏል።

”ድርድሩ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ስለ ግድቡ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን በግልጽ እንዲረዳ ያደረገ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የግድቡ የውሃ ሙሊት ስራና አጠቃላይ ኃይል የማመንጨቱ ተግባር በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ጉልህ ተጽዕኖ ሳያሳድርና የኢትዮጵያን ጥቅም ሳይጎዳ እንዴት መከናወን እንዳለበት የተደረሰውን መግባባትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ሐምሌና ነሃሴ ዋነኛ የሙሊት ስራ ማከናወኛ ወራቶች እንዲሆኑ የተመረጡበት ምክንያት የአባይ ወንዝ ከፍተኛ የውሃ ፍሰት ስለሚኖረው እንደሆነም ገልጸዋል።

ሶስቱ አገሮች የሚገጥማቸውን ድርቅ በኃላፊነት መንፈስ በጋራ ለመከላከል መስማማታቸውም ለወንዙ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

አገሮቹ የደረሱበትን ቴክኒካዊ መግባባት ወደ ህግ ማዕቀፍ ለማሸጋጋር በሚዋቀረው ዘጠኝ አባላት ያለው ቡድን የሚሳተፉ ሶስት ግለሰቦች መመረጣቸውንም ሚኒስትሩ አውስተዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ቡድኑ የሚያጸድቀውን የህግ ማዕቀፍ ለመፈረምና አጠቃላይ የድርድር ሂደቱን ለማጠናቀቅ እ.አ.አ በመጪው ጥር 28 እና 29 በዋሽንግተን ዲሲ ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸው ይታወሳል።